መንግስት የጋምቤላ ከተማን ሙሉ ለሙሉ ከአማጺያን ነጻ ማውጣቱን አስታወቀ
የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው መግባታቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል
"ሸኔ እና "የጋምቤላ ነጻ አውጭ ግንባር" ትናንት በከተማዋ ተኩስ መክፈታቸው ተገልጾ ነበር
የጋምቤላ ከተማን ትናንትና ተኩስ ከፍተው ከነበሩ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ነጻ ማውጣቱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡
የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ የጋምቤላ ከተማን መንግስት “ሸኔ” ራሱን ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራውና ከጋምቤላ ነጻ አውጭ ግንባር ነጻ ማውጣቱን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ከአማጺያኑ ነጻ እንደወጣች ያነሱት አቶ ኡገቱ የማጥራት ስራ ብቻ እንደሚቀር ለአል ዐይን ገልጸዋል።
የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው መግባታቸው የተነገረ ሲሆን አሁን ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ መረጋጋቷ ተገልጿል።
"ሸኔ እና "የጋምቤላ ነጻ አውጭ ግንባር" ትናንት በከተማዋ ተኩስ መክፈታቸው ተገልጾ ነበር
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዑመድ ትናንት ተኩስ የከፈቱት ቡድኖች የርዕሰ መስተዳድሩን ጽ/ቤት እንደተቆጣጠረ ተደርጎ የተናፈሰው ወሬ ሀሰት መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።
በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በክልሉ የሚገኙ የፀጥታ ሀይሎች ባካሄዱት ቅንጅታዊ ማጥቃት ከተማውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉንም ገልጸዋል።
ተከፍቶ በነበረው ተኩስ ከሁሉም ወገን ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በከተማው ተኩስ ከፍተው በነበሩ ሃይሎች ላይ የፀጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ ከተማውን ማረጋጋት ተችሏል ብለዋል።