የጋምቤላ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በዜጎች ላይ ያልተመጣጠነ እርምጃ መወሰዳቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
በጋምቤላ ከተማ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት አሁንም ዜጎች አልተረጋጉም ተብሏል
የክልሉ መንግስት የዜጎችን ደህንነት እንዲያስከብርም ተቋሙ አሳስቧል
በጋምቤላ ከተማ በዜጎች ላይ ያልተመጣጠነ እርምጃ መወሰዱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ገለጸ፡፡
ኢሰመኮ መምሻውን ባሳለፍነው ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ/ም በጋምቤላ ከተማ ከተፈጠረው ጉዳይ ጋር ተያይዞ እየተከሰቱ ባሉ ድርጊት ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ድርጅቱ እንዳለው ከሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል እና መደበኛ ፖሊስ በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ምክንያት ነዋሪዎች ከሕግ ውጭ ግድያ ስለመፈጸሙ መረጃዎች ደርሰውኛል ብሏል፡፡
በተለይም በጥቃቱ ተሳትፈዋል ወይም ተባብረዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ቤት ለቤት በመሄድ ጭምር ግድያዎች እንደተፈጸሙ ኢሰመኮ ከምስክሮችና የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃዎች ጭምር ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት መቻሉን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የሰዎችን ደኅንነትና የከተማዋን ሰላም ማረጋገጥ የመንግስት ቀዳሚው ተግባር መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚወሰዱ እርምጃዎች በሙሉ የሰብአዊ መብቶች መርሆች ሊከተሉ እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶ/ር ዳንኤል በተለይም የፀጥታ ኃይሎች ሕይወት ሊያጠፋ ከሚችል ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡና በፀጥታ ኃይሎች የተወሰዱ ሕገ ወጥ ተግባራት ላይ በአስቸኳይ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም አሳስበዋል።
በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋት እስከ ምሽት የቀጠለ ግጭት እና የፀጥታ እና የደኅንነት ችግርን ተከትሎ ለአንድ ቀን የከተማዋ የመንግሥት አገልግሎቶች፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች እና ሌሎችም አገልግሎቶች ተቋርጠው መዋላቸው ይታወሳል።
ጥቃቱ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች የተከፈተ እንደነበር እና ክስተቱ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ የክልሉ መንግሥት አሳውቋል።
በዕለቱ የመንግሥት የፀጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ የከተማዋ ፀጥታ የተረጋጋ እና በአሁኑ ወቅት የሀገር መከላከያ ሠራዊት በከተማው የሚገኝ ቢሆንም እስከ አሁንም ድረስ የተሟላ መረጋጋት አለመስፈኑን፣ የነዋሪዎች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ አለመጀመሩን፣ እንዲሁም በተለይም የንግድ አካባቢዎችን ጨምሮ በአንዳንድ ስፍራዎች ዘረፋ እንደተፈጸመ ነዋሪዎች ለኢሰመኮ መናገራቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።