በጋምቤላ ከተማ ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ተነሳ
ከአንድ ወር በፊት በጋምቤላ ከተማ አማጺያን ተኩስ ከፍተው እንደነበር መንግስት መግለጹ ይታወሳል
የክልሉ መንግስት ተኩስ የከፈቱት "ሸኔ እና "የጋምቤላ ነጻ አውጭ ግንባር" መሆናቸውን ገልጾ ነበር
በጋምቤላ ከተማ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከቀናት በፊት ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ተነሳ፡፡
የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት፤ እገዳው ተጥሎ የነበረው ከወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ነው እንደሆነ ገልጿል፡፡ ይሁንና አሁን የሰዓት እላፊ ገደቡ መነሳቱ ተገልጿል፡፡
ከአንድ ወር በፊት በጋምቤላ ክልል አማጺያን ጥቃት ሰንዝረው የሰው ህይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ የክልሉ መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡
የክልሉ መንግስት "ሸኔ እና "የጋምቤላ ነጻ አውጭ ግንባር" ሰኔ ወር መጀመሪያ ሳምንት አካባቢ ተኩስ መክፈታቸውን ገልጾ ነበር፡፡
ተኩስ በተከፈተበት ወቅት ርዕሰ መስተዳድር ኡመድ ኡጁሉ፤ በጋምቤላ ከተማ በነበረው ተኩስ በከተማው በሚገኙ የመንግስት ተቋማት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡
አል ዐይን አማርኛ በወቅቱ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተኩስ በተከፈተበት ወቅት ወደ ስራ አለመሄዳቸውንና ተኩስ እየሰሙ እነደነበርም ተናግረው ነበር፡፡ በወቅቱ ክልሉ በአማጺያን ቁጥጥር ስር ውሏል መባሉ ርዕሰ መስተዳድር ዑመድ ውሸት ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በወቅቱ ከነበረው ችግር ጋር በተያያዘ በጋምቤላ ከተማ በዜጎች ላይ ያልተመጣጠነ እርምጃ መወሰዱን ገልጾ ነበር።
ኢሰመኮ ያልተመጣጠነ ነው ያለው ከሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል እና መደበኛ ፖሊስ በነዋሪዎች ላይ ተወስዷል ያለውን የግድያ ርምጃ ነበር።