በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች እና እስሮች "እጅግ አሳሳቢ" መሆናቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
የፌደራል መንግስት በአማራ ክልል በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ መኖሩን እና ይህንን በመደበኛው የህግ ስርአት መቆጣጣር እንደማይቻል በመግለጽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል
የእስርን ጉዳይ በተመለከተ ኢሰመኮ ኮማንድ ፖስቱ በይፋ ከገለጻቸው እስሮች እና ቦታዎች ውጭ በአማራ ክልል፣ በአሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የዘፈቀደ እስር ተፈጽሟል ብሏል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ባወጣው ሪፖርት በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች እና ከህግ አግባብ ውጭ የሆኑ ግድያዎች እና እስሮች "እጅግ አሳሳቢ" መሆናቸውን ገልጿል።
በአማራ ክልል ያለው የትጥቅ ግጭት ወደ የተለያዩ ወረዳዎች መስፋፋቱን የገለጸው ኢሰመኮ በተለይም በክልሉ በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳትም ተስፋፍቷል ብሏል።
ከህግ አግባብ ውጭ "በመንግስት የጸጥታ አካላት እየተፈጸሙ ያሉት ግድያዎች እጅግ አሳሳቢ" መሆናቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ ጠቅሷል።
የግድያ እርምጃ ሰለባ የሆኑት "ለምሳሌ ከሐምሌ 24 እስከ ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በተለይም በአዴት፣ ደብረማረቆስ፣ በደብረ ታቦር፣ ጅጋ፣ ለሚ፣ ማጀቴ፣ መራዊ፣ መርጦ ለማርያምና ሸዋ ሮቢት ከተሞች ተስፋፍተው በተፈጸሙ ከሕግ/ፍርድ ውጪ የሆኑ ግድያዎች ሰለባ ከሆኑ ሰዎች መካከል ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ የተያዙ ሰዎች፣ በግጭቱ ወቅት መንገድ ላይ የተገኙ እና ያልታጠቁ ሰዎች፣ “የጦር መሣሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል የተያዙ ሰዎች ናቸው ብሏል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ የሰዓት እላፊ ገደቦችን ተላልፈው የተገኙ ሲቪል ሰዎችና በቁጥጥር ስር የዋሉ የታጣቂው ቡድን (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚታወቀው) አባላት የሚገኙበት መሆኑን የገለጸው ኢሰመኮ የተሟላ ምርመራ እንደሚያደርግ ገልጿል።
የእስርን ጉዳይ በተመለከተ ኢሰመኮ ኮማንድ ፖስቱ በይፋ ከገለጻቸው እስሮች እና ቦታዎች ውጭ በአማራ ክልል፣ በአሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የዘፈቀደ እስር ተፈጽሟል ብሏል።
ኢሰመኮ ግጭቱ በሰላሚ መንገድ እንዲፈታም አሳስቧል።
የፌደራል መንግስት በአማራ ክልል በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ መኖሩን እና ይህንን በመደበኛው የህግ ስርአት መቆጣጣር እንደማይቻል በመግለጽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።
አዋጁ ከጸደቀ በኋላ መንግስት አብዛኞቹን የክልሉን ከተሞች ከስጋት ነጻ ማድረጉን እና አሁን ላይ ክልሉ ወደ አንጻራዊ ሰላም እየተመለሰ መሆኑን ቢገልጽም ራቅ ባሉ ወረዳዎች ግጭቶቹ አልቆሙም።
የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ግጭቱ እንዲቆም እና በንግግር መፍትሄ እንዲያገኝ በተለያየ ጊዜ ጥሪ አቅርበዋል።