በአማራ ክልል በተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ ላይ ማሻሻያ ተደረገ
በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻልና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች እንዳይዳከሙ ነው ሠዓት እላፊ ማሻሻያው የተደረገው
የሰዓት እላፊ ገደቡ ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋት 11፡30 ድረስ ማሻሻያ መደረጉን ክልሉ አስታውቋል
በአማራ ክልል ተጥሎ በነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ላይ ማሻሻያ መደረጉን የክልሉ የመንግሥት አስታወቀ።
የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃለፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በሰጡት መግለጫ፤ የክልሉ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ በተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ ማሻሻያ ማድረጉን ገልፀዋል።
የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች እንዳይዳከሙና በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዲያስፖራዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማሻሻያ ተደርጓል።
በዚህም መሰረት ከዚህ ቀደም ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ጠዋት 12 ሰዓት የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደቡ ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋት 11፡30 ድረስ ማሻሻያ መደረጉን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ለ6 ወረት ተፈጻሚ የሚደረግ የአስቸኳይ ጊዝ አዋጅ ባሳላፍነው ጥቅምት ወር ላይ መታወጁን ተከትሎ ክልሎች የሰዓት እላፊ ገደቦችን ሲጥሉ የቆየሱ ሲሆን፤ የአማራ ክልልም የሰዓት እላፊ ገደብ ከጣሉ ክልሎች ውስጥ አንዱ ነው።
የኦሮሚያ ክልልም ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት 11፡30 ድረስ ጥሎ የነበረ ሲሆን፤ ከቀናት በኋላ የጣለውን የሰዓት እላፊ ማሳቱ ይታወሳል።
ትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ባለፈው ጥቅምት 24 አንድ አመት አስቆጥሯል።
የኢትዮጵያ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የትግራይን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ በርካታ ቦታዎች መቆጣጠር ቢችልም ከ8 ወራት በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ጦሩን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወሳል።
መንግስት ይህን ቢልም፤ ህወሓት የመንግስት ጦር እንዲወጣ ማድረጉን በወቅቱ ገልጾ ነበር። ህወሓት ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት በርካታ ቦታዎች መቆጣጠርም ችሎ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሰት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኋላ በህወሃት ተይዘው የነበሩ በርካታ የአማራ እና የአፋር ክልል ቦታዎች ነጻ ወጥተዋል።
መንግስት የህወሓት ሀይሎችን በማሸነፍ ይዘዋቸው ከነሩ ቦታዎች እንዲወጡ ማድረጉን ሲገልጽ ህወሓት በአንጻሩ “ለሰላም እድል ለመስጠት” ሲባል ከአማራ እና አፋር ክልሎች ተዋጊዎቹን ማስወጣቱን ይገልጻል።
ከአንድ አመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነቱ በሺዎች ሲገደሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለው ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል።