በአማራ ክልል ሁለት አጎራባች ዞኖች መካከል በሚገኙ ቀበሌዎች የተቀሰቀሰው ውጊያ እስካሁን አልቆመም
የፌዴራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት በስፍራው መድረሳቸው ተነግሯል
ውጊያው በጅሌ ጥሙጋ እና ኤፍራታና ግድም ወረዳ አጎራባች ቀበሌዎች ያጋጠመ ነው
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ ቀበሌዎች ግጭት መቀስቀሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
ግጭቱ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ በጤ ቀበሌን እና በኤፍራታና ግድም ወረዳ አርሶ አምባ (ዘምቦ) ቀበሌን በሚያጎራብቱ አጎራባች አካባቢዎች (ጎጦች) ያጋጠመ ነው፡፡
ቀበሌዎቹ ከአዲስ አበባ ደሴ በሚያልፈው አውራ የአስፓልት መንገድ ላይ በሰንበቴ እና ጀውሃ ከተሞች መካከል የሚገኙ ናቸው፡፡
ከትናንት ምሽት ጀምሮ በአጎራባች የቀበሌዎቹ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጥ እንዳለ ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም የማያቋርጥ የጥይት ድምፅ እየሰሙ መሆኑን ገልፀዋል።
ግጭቱ የሰብል ዝሪት ላይ ከብቶች ተለቀዋል በሚል መቀስቀሱን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ በተኩስ ልውውጡ የሰው ህይወት መጥፈቱንም ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የደረሰው ተጨማሪ ጉዳት እንዳለ አብራርተው ዘርዝረው አልገለጹም። የተኩስ ልውውጡ ዛሬም መቀጠሉ የተሰማ ሲሆን በረሃ እና ዋዠና በተባሉ የአርሶ አምባ (ዘምቦ) ቀበሌ አካባቢዎች ከባድ ውድመት መድረሱን የአል ዐይን የመረጃ ምንጮች አመልክተዋል፡፡
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የኤፍሬታ ግድም ወረዳ ነዋሪ ከትናንት ረፋድ ጀምሮ በሁለቱ ቀበሌዎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እንዳለ ገልጸው፤ በዚህም ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል፡፡
"የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች" በአካባባቢው በስፋት እንደሚንቀሳቀሱና እንደሚሰለጥኑ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሸኔ ታጣቂዎች ወደ መኖሪያ መንደሮች ዘልቀው በመግባት ጥቃት በማድረስ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ለቀው ወደ አጎራባች ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በመሰደድ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ መንግስት ተጨማሪ ጸጥታ አስከባሪ ሀይል እንዲልክላቸውም ነው ነዋሪዎቹ የጠየቁት፡፡
የክልሉ ልዩ ኃይል ሁኔታዎችን ለማረጋጋት በማሰብ ግጭቱ ወዳለባቸው አካባቢዎች ገብቷል፡፡ ሆኖም የታጣቂዎቹ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ግጭቱን ማስቆም አልቻለም እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ፡፡
አል ዐይን አማርኛ ስለ ግጭቱ የጠየቃቸው የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ መሐመድ ግጭቱ ትናንት በነበረበት አካባቢ ቢቆምም በሌሎች አካባቢዎች የሚሰማ የተኩስ ልውውጥ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ግጭቱ አካባቢ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አህመድ የተረጋጋ ሁኔታ እንደሌለ በመጠቆም የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላት ለመግባትና ሁኔታዎችን ለማረጋጋት፤ ወደ ግጭቱ የሚገቡ ሰዎችንም ለማስቆም ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃዲቅ በበኩላቸው በተጠቀሱት ቦታዎች ግጭት መቀስቀሱን ተናግረው ግጭቱ ሳይባባስ ለማስቆም ተጨማሪ ሀይል ወደ ስፍራው መላኩን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል በሁለቱ ዞኖች ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ጦርነቶች የተካሄዱ ሲሆን አጣዬ ከተማ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መውደሟ ይታወሳል፡፡
ከሁለት ወራት በፊት በዚሁ አካባቢ በተፈጠረ ተመሳሳይ ጥቃት በኤፍራታና ግድም ወረዳ ያለች ሞላሌ የተባለች መንደር ሙሉ ለሙሉ መውደሟም የሚዘነጋ አይደለም፡፡