መንግስት በ 5 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የጣለውን እገዳ እንዲያነሳላቸው ኢሰመኮ ጠየቀ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተቋማቱ የፈጸሟቸው ዝርዝር የህግ ጥሰቶች ባልገለጸ ሁኔታ መታገዳቸው አሳስቦኛል ብሏል
ድርጅቶቹን የሚቆጣጠረው መንግስታዊ ተቋም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን 5 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን አደግዷል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መንግስት በአምስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ እያደረገ ያለውን ምርመራ አጠናቆ እገዳውን እንዲያነሳላቸው ጠይቋል።
ማህበራቱን በሚቆጣጠረው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በኅዳር ወር 2017 ዓ.ም. የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማእከል፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እና ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ የተባሉ 3 በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አግዶ እንደነበር ይታወሳል።
ባለሥልጣኑ በ3ቱም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የጣለውን እግድ አንስቶ የነበረ ቢሆንም ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በድጋሚ በጻፈው ደብዳቤ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማእከልን እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶችን ከማንኛውም እንቅስቃሴ ለ2ተኛ ጊዜ አግዷል፡፡
በተጨማሪም በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሠሩት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል መታገዳቸው ታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ እየተጣለ የሚገኝውን እግድ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ሁሉም በሚባል ደረጃ “ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መሥራት ሲገባው ከዓላማው ውጭ በመንቀሳቀስ የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ ተግባራት ላይ መሰማራቱ” የሚል ተመሳሳይ የእገዳ ደብዳቤ የደረሳቸው መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ ብሏል፡፡
በዚህም ድርጅቶች ተመሳሳይ ይዘት ባለው እና ተቋሟቱ የፈጸሟቸውን ከባድ የሕግ ጥሰቶች በዝርዝር ባላስቀመጠ ደብዳቤ መታገዳቸው አሳሳቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ነው ያለው፡፡
ኮሚሽኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ ተደጋጋሚ እገዳዎች የሲቪክ ምኅዳሩን በማጥበብ በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር እንደሚያሰጋው ገልጿል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የምርመራ ሥራዎቹን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻችም ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የመብት ጥበቃ ላይ የሚሰራው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በትላንትናው እለት ስለመታገዱ መግለጫ አውጥቶ ነበር
በመግለጫው "ድርጅታችን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከተቋቋመበት አላማ ውጭ በየትኛውም ያልተገባ ወይም ከህግ የሚጻረር እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ አያውቅም" ብሏል።