የአቶ ልደቱ እና የዶ/ር ሁሴን ከድር የዋስትና መብት በአስቸኳይ ሊፈቀድ እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳሰበ
የክልሉ ሥራ አስፈጻሚና የፍትሕ አካላት የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበሩን እንዲያረጋግጡም ጠይቋል
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበሩ እንዲረጋግጥም ጥሪ አቅርቧል
የአቶ ልደቱ እና የዶ/ር ሁሴን ከድር የዋስትና መብት በአስቸኳይ ሊፈቀድ እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳሰበ
በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸውና የዋስትና ሁኔታውን አሟልተው ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠላቸው ሰዎች በእስር እንዲቆዩ መደረጉ “ፍትሕን የሚያጓድልና ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ ተግባር ነው”ሲል ከአሁን ቀደም ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበሩ እንዲረጋግጥ ጥሪ አቀረበ፡፡
ኮሚሽኑ የክልሉ ሥራ አስፈጻሚና የፍትሕ አካላት የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበሩን እንዲያረጋግጡም ጠይቋል።
ስለ ሁኔታው ለሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች በማሳወቅ ክትትሉን መቀጠሉን ያስታወቀው ኮሚሽኑ የተወሰዱ አበረታች እርምጃዎች ቢኖሩም በተለይ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው አሁንም ድረስ በእስር የሚገኙ ሰዎች አሉ ብሏል።
ከነዚህ መካከል የአቶ ልደቱ አያሌው እና የዶ/ር ሁሴን ከድር ጉዳይ “አፋጣኝ እልባት የሚሻ መሆኑንም” ነው ኮሚሽኑ ያሳሰበው።
አቶ ልደቱ ከሐምሌ18 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ክስ ተመስርቶባቸው አሁንም በድጋሚ ባቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል።
ፎቶ፡ ከማህበራዊ ሚዲያ
አደረግሁት ባለው ምርመራ መሰረት “በአቶ ልደቱ ላይ የቀረቡት ክሶች የዋስትና መብት የማያስከለክሉ ናቸው” ያለው ኮሚሽኑ የጤንነታቸው ሁኔታ ማስረጃዎች የዋስትና መብት ጥያቄውን በአፋጣኝ ተግባራዊ ማድረግን አስፈላጊነት ያስረዳሉ ብሏል።
በመሆኑም የአቶ ልደቱ የዋስትና መብት በአስቸኳይ ሊፈቀድ እንደሚገባ ነው ያሳሰበው።
በሌላ በኩል ዶ/ር ሁሴን ከድር ከሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
የዋስትና መብት ፈቅዶላቸዉ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ከሰጠው የአጋርፋ ወረዳ ፍርድ ቤት በተጨማሪ የፌደራል ዐቃቤ ሕግም ክስ ለማቅረብ የሚያበቃ ማስረጃ አለማግኘቱን ጠቅሶ የምርመራ መዝገቡን ዘግቶ ነበር።
ሆኖም ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ ፖሊስ ለኮሚሽኑ እንዳሳወቀው በተጨማሪ ወንጀል በመጠርጠራቸው አሁንም በእስር ላይ ናቸው እንደኮሚሽኑ ገለጻ፡፡
ዶ/ር ሁሴን ከድር አብዛኛውን የእስር ጊዜ የቆዩት በአጋርፋ እስር ቤት ነበር፡፡
ሆኖም ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተወስደው አሁንም በኦሮሚያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ፡፡
ይህን ተረድቻለሁ ያለው ኮሚሽኑም “ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ወዲህ ከቤተሰቦቻቸው አለመገናኘታቸው አሳስቦኛል”ብሏል።
ስለሆነም በአስቸኳይ በቤተሰባቸው ሊጎበኙ ከመገባቱም በተጨማሪ “ሊያስከስስ የሚችል አሳማኝ ክስ ካለ በአፋጣኝ ሊቀርብ፣አሊያም ከእስር ሊለቀቁ ወይም የዋስትና መብታቸው በአስቸኳይ ሊከበር” እንደሚገባም አሳስቧል ኮሚሽኑ።
“የዋስትና መብት በሕገ መንግስቱና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የተረጋገጠ መሰረታዊ መብት ነው” ያሉት ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በሕግ በግልጽ ከተመለከቱ ሁኔታዎች በስተቀር የዋስትና መብት በተቀላጠፈ አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለ4 ወራት ያህል በእስር የቆዩት የአቶ ለሚ ቤኛ እና የአቶ ዳዊት አብደታ የዋስትና መብት እንዲረጋገጥ ለተሰጠው ትክክለኛ ውሳኔ እውቅና ሰጥቷል፡፡