የጋምቤላ ክልል ኢሰመኮ ከአንድ ሳምንት በፊት ያወጣውን ሪፖርት ውድቅ አደረገ
የኢሰመኮን ሪፖርት የአንድ ወገንና የክሉን የጸጥታ ሀይሎች የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳንስ ነውም ተብሏል
ኢሰመኮ ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ ከ50 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን ይፋ አድርጓል
የጋምቤላ ክልል ኢሰመኮ ከአንድ ሳምንት በፊት ያወጣውን ሪፖርት ውድቅ አደረገ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል ሰኔ ወር ላይ 2014 ዓ.ም በጋምቤላ ከተማ በኦነግ ሸኔ እና ጋምቤላ ነጻ አውጪ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት ንጹሃን ዜጎች መጎዳታቸውን አደረኩት ባለው የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በጋምቤላ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች " የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እና መሣሪያ በቤታችሁ እንዳለ ተጠቁመናል፤ የደበቃችሁትን መሣሪያ አውጡ " በሚል ምክንያት ሴቶችና የአእምሮ ሕመምተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች በተናጠል እና በጅምላ ከፍርድ ውጪ መገደላቸውን ገልጿል፡፡
እንዲሁም ቢያንስ 25 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ከመድረሱ ባለፈ በበርካታ ሰዎች ላይ የመደብደብና የማሰቃየት ተግባር መፈጸሙን በተጨማሪም በኦነግ ሸኔ፣ በጋነግ፣ በክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ ሚሊሻዎች እና ተባባሪ ወጣቶች በበርካታ ሰዎች ላይ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ እንተፈጸመ በምርመራዩ አረጋግጫለሁ ብሎም ነበር ኢሰመኮ፡፡
የጋምቤላ ክልል አስተዳድር ባወጣው መግለጫ የኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት ላንድ ወገን ያደላ እና ትክክለኛነት የሚጎደለው ሪፖርት እንደሆነ ገልጿል፡፡
ክልሉ እንዳለው ሪፖርቱ የአንድ ክልል የፀጥታ ተቋምን ከተራ የአሸባሪ ቡድን ተላላኪ ጋር በአንድነት ያየ፤ በክልልና በአገር ላይ ይደርስ የነበረ ከፍተኛ ጥቃት በመቀልበስ ሂደት የህይወት መስዋዕትነት የከፈለውን የፀጥታ ተቋሙን በጅምላ የፈረጀ፤ የተገኘውንም ድል በዜሮ ያባዛ በመሆኑ የኢሰመኮን ሪፖርት አልቀበለውም ብሏል።
ክልል አክሎም የኢሰመኮ ሪፖርት በመረጃ ላይ ያልተመሰረተ ሚዛናዊ ያልሆነ ፣መረጃው ከኦነግ ሸኔና ህወኃት ደጋፊዎች እንዲሁም በተለያዩ ወንጀሎች ሲጠረጠሩ ከነበሩ ግለሰቦች የተወሰደ እንደሆነም አስታውቋል፡፡