ኢሰመኮ ከዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት የደረጃ “A” እውቅና ማግኘቱን አስታወቀ
ኢሰመኮ ከኅዳር 2006 ዓ.ም ጀምሮ በ“B (2ኛ ደረጃ) ላይ ቆይቷል
ኢሰመኮ የደረጃ “A” እውቅና እንዲያገኝ አስተዋጽዖ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርቧል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ከዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት የደረጃ “A” እውቅና ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ኢሰመኮ ለአልአይን በላከው መግለጫ የዓለም አቀፉ የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት ከጠንካራ የግምገማ ሂደት በኋላ የሚሰጠውን (Global Alliance of National Human Rights Institutions (GANHRI)) የደረጃ “A” (አንደኛ ደረጃ) እውቅና አግኝቻለሁ ብሏል፡፡
ይህ የአንደኛ ደረጃ እውቅና ማግኘቱ ኮሚሽኑ የፓሪስ መርሆችን ሙሉ በሙሉ ማሟላቱን የሚያሳይ መሆኑንም ኮሚሽኑ አክሏል።
የዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (GANHRI) የእውቅና ገምጋሚ ንዑስ ኮሚቴ ከፈረንጆቹ ከጥቅምት 8 እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2021 ባደረገው ጉባዔ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጥምረቱ የተከናወነውን የግምገማ ሂደት ማለፉን ተገልጿል፡፡
ይሄንንም ተከትሎ፣ ለኮሚሽኑ የደረጃ “A” እውቅና (አንደኛ ደረጃ እውቅና - “A” Status Accreditation) መስጠቱን አስታዉቋል ብሏል፡፡
ጥምረቱ ኮሚሽኑ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም የሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ እና ለማስፋፋት እየተጫወተ ያለውን ሚና አድንቆ፣ በተለይም በፈረንጆቹ በኅዳር ወር 2013 በጥምረቱ ተለይተው የነበሩ ጉድለቶችንም ለማስተካከል ያደረገውን ጥረት አመስግኗል።
የዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (GANHRI) 118 ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት የሆኑ አባላት ህብረት ሲሆን ከፓሪስ ስምምነቶች ጋር የተጣጣሙ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት መመስረትን እና መጠናከርን የሚያበረታታ ነው።
በፈረንጆቹ በ1993 የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ያጸደቀውና በአጭሩ የፓሪስ መርሆች ተብሎ የሚጠራው የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት መርሆች የተቋማቱን ተዓማኒነትና ብቃት ለመገምገም የሚያገለግል ሰነድ ነው፡፡
ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋማት በሕግ፣ በአሰራር፣ በአባልነት፣ በፖሊሲ እንዲሁም በፋይናንስ ገለልተኛ እና ከጣልቃ ገብነት ነጻ እንዲሆኑ ይደነግጋል።
በፓሪስ መርሆች መሰረት ተቋማቱ ኃላፊነት እና ሥልጣን ስፋት፣ የሰው ሃብታቸውን ብዝኃነት፣ የተግባራትና እና የገንዘብ አቅም፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና ትብብር የሰብዓዊ መብት ተቋማት መገምገሚያ መስፈርቶች መካከል ናቸው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅታዊ አቋሙን እና አሰራሩን ለማሻሻል ያስቻሉ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ 2 የተቋሙን የአሰራር እና የበጀት አስተዳደር ነፃነት አረጋግጧል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም አዲሱ አዋጅ በምርጫ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል ስራዎችን እንዲያከናውን እና ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የእስር ቦታዎችን መጎብኘት ማስቻሉን ተቋሙ ገልጿል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ያገኘው እውቅና ትልቅ እመርታ መሆኑን አመልክተው “ኮሚሽኑ ከኅዳር 2006 ዓ.ም ጀምሮ ከነበረበት “B (2ኛ ደረጃ) ወደ “A” (አንደኛ ደረጃ) ለማደጉ እውቅና መሰጠቱ ኮሚሽኑ ገለልተኛ፣ ውጤታማ እና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን የሚያሟላ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም መሆኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል፡፡
ኢሰመኮ ወደ ደረጃ “A” (አንደኛ ደረጃ) መሸጋገሩ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት እና በስሩ በሚገኙ ተቋማት ውስጥ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የጠቅላላ ጉባዔ አካላት ውስጥ ነጻ ተሳትፎ እንዲኖረው ያስችላል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም እውቅናው በዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ጥምረት (GANHRI) ውስጥ አባል ለመሆን፣ድምጽ ለመስጠት እና የአመራር ቦታዎችን ለመያዝ ብቁ እንደሚያደርገው ዶክተር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡