ኤርትራ፤ የትግራይ ግጭትን በተመለከተ የኢሰመኮ እና የተመድን የጋራ ሪፖርት እንደማትቀበል አስታወቀች
ምርመራው ከምስክሮች ተዓማኒነት፣ ከተደረገበት ጊዜ እና ከሸፈናቸው ቦታዎች አንጻር ውስንነቶች እንዳሉበትም ነው ኤርትራ ያስታወቀችው
የምርመራ አካላቱን ገለልተኛነት ያጠየቀችው ኤርትራ በምርመራው አካሄድና ትክክለኛነት ላይ ጥያቄዎችን አንስታለች
የትግራይ ግጭትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተመድ ጣምራ የምርመራ ቡድን ዛሬ ይፋ ያደረጉትን ሪፖርት እንደማትቀበል ኤርትራ አስታወቀች፡፡
የምርመራ አካላቱን ገለልተኛነት ያጠየቀችው ኤርትራ በምርመራው አካሄድና ትክክለኛነት እንዲሁም ህጋዊነት ላይ ጥያቄዎችን አንስታለች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ሪፖርቱን የተመለከተ ዝርዝር መግለጫ አውጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በምርመራ ሪፖርቱ የተወሰኑ ይዘቶች ላይ ትልቅ ቅሬታ እንዳለው ገለጸ
በመግለጫው በዝርዝር የተጠቀሱ ጥያቄዎችን በመርማሪ ተቋማቱ እና በአካሄዱ ላይ ያነሳው ሚኒስቴሩ እንከን ያላቸውን ነጥቦች አስቀምጧል፡፡
ኢሰመኮ በዋናነት ደግሞ ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ (ዶ/ር) ለኤርትራ “ጥላቻ” እንዳላቸው በማተት የሚጀምረው መግለጫው “ይህም የሂዩማን ራይትስ ዎች (HRW) የአፍሪካ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት የኤርትራን የማዕድን ዘርፍ በተመለከተ ባወጡት መግለጫ ተንጸባርቋል” ይላል፤ መግለጫው በወቅቱ ተቋሙ ይከተል የነበረውን “የስርዓት ለውጥ” እንደሚያንጸባርቅ በመጠቆም፡፡
ጥቂት የማይባሉ ኤጀንሲዎቹ በግጭቱ “የህወሓት ደጋፊ” ሆነው ሳለ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ የምርመራው አካል እንዲሆን የመጋበዙን ህጋዊነትና ገለልተኛነትንም ያነሳል መግለጫው፡፡ የድርጅቱ የበላይ አካላት ጭምር “አይታመኑም”ም ነው የሚለው መግለጫው፡፡ ለዚህም ከድርጅቱ ያፈተለኩ ናቸው ያላቸውን መረጃዎችና ሰባት ሰራተኞቹ ከኢትዮጵያ መባረራቸውን ዋቢ በማድረግ ያስቀምጣል፡፡
የቀድሞው የቢሮው ኃላፊ ማርክ ሎው ኩክ በወቅቱ ሰጥተውት የነበረው መግለጫ ይህንኑ የኤጀንሲዎቹን አቋም አጠቃሎ የሚያሳይ እንደሆነም የሚገልጸው፡፡
የትግራይ ግጭት ተሳታፊዎች “በተለያየ መጠን” የሰብአዊ መብቶችን መጣሳቸውን የምርመራ ቡድኑ ገለፀ
በተመሳሳይ ሁኔታ ቢሮው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው ዓመት ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ/ም ህግ የማስከበር ዘመቻ እንዲጀመር ማዘዛቸውን ተከትሎ “የመከላከያ ሰራዊቱ፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻው የህወሓት ኃይሎችን ማጥቃት ጀመሩ” ሲል “የተዛባ” ረቂቅ ሪፖርት አውጥቶ እንደነበርም አስታውሷል፤ ህግ የማስከበር ዘመቻው ጥቅምት 24 ሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ መጀመሩን በመጠቆም፡፡
‘መብረቃዊ’ በሚል በህወሓት ኃይሎች ሲገለጽ የነበረው ድንገተኛ ጥቃት አንድም በኢትዮጵያ መልሶ ስልጣን ለመያዝ ሁለትም ወደ ኤርትራ ለመስፋፋት በማሰብ የተፈጸመ ነውም ይላል፡፡
ይህን መሰረታዊ እውነታ ለመቀበል ያልፈገውን የምርመራ ቡድን ሪፖርት ለመቀበል እንደሚቸገርም ነው ያስታወቀው፡፡
ኤርትራን የተመለከቱ መረጃዎች ተዛብተው መቅረባቸውን የሚያትተው መግለጫው ምርመራው ከምስክሮች ተዓማኒነት፣ ከተደረገበት ጊዜ እና ከሸፈናቸው ቦታዎች አንጻር ውስንነቶች ያሉበት ነው ይላል፡፡
የኤርትራን ጦር መዳኘትም ሆነ ለተጎጂዎች ፍትህ መስጠት ከተፈለገ የሚቻለው፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በሌሎች በኤርትራ ህግ መሰረት ገለልተኛ እና እውነተኛ ምርመራን ለማድረግ በሚችሉ አካላት እንደሆነም ያስቀምጣል መግለጫው፡፡
በትግራዩ ግጭት፤ “ዘር የማጥፋት ወንጀል” መፈጸሙ አልተረጋገጠም ተባለ
ምንም ዐይነት ማረጋገጫና ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው የሚላቸውን የአክሱምን ጭፍጨፋና ሌሎች ጾታዊና በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ ጥቃቶችንም ያነሳል፡፡
በእነዚህ ምክንያት ጣምራ ሪፖርቱ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ፤ ኤርትራ ፈርማ ህግ ያደረገቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ማክበሯን እንደምትቀጥል አስታውቋል፡፡
እነዚህን ህጎች በሚጥሱ የሰራዊት አባላት ላይ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂ እንደሚያደርግም ነው ያስታወቀው፡፡