የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርሆዎችን ባከበረ መልኩ እየተተገበረ አይደለም - ኢሰመኮ
“በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸው ይገመታል”ም ብሏል ኮሚሽኑ
የታሰሩ ሰዎችን ብዛት በሚመለከት የተሟላ መረጃ ለማግኘት አለመቻሉንም ነው ኢሰመኮ የገለጸው
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መተግበር ባለበት መንገድ እየተተገበረ አይደለም አለ፡፡
ኢሰመኮ አደረግሁ ባለው ክትትል በተለይም አዋጁ “የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነፃ መሆን” የሚሉትን የሰብአዊ መብት መርሆዎች ባከበረ መልኩ አለመተግበሩን አስታውቋል።
አዋጁ ከታወጀበት ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችን የተመለከቱ መረጃ ለማሰባበሰብ አለመቻሌ አሳስቦኛል ሲል መግለጫ ያወጣው ኢሰመኮ በአዲስ አበባ በቂርቆስ እና በየካ ክፍለ ከተሞች ማቆያዎችን ለጎብኘት እና ከፖሊስ አካላት ጋር ለመወያየት ቢችልም ‘ከበላይ ትእዛዝ አልመጣልንም’በሚል ምክንያት በአዲስ ከተማ፣ በልደታ፣ በጉለሌ፣ በቦሌ እና በአራዳ ክፍለ ከተሞች ይህን ለማድረግ አለመቻሉን ገልጿል፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 714፣ በድሬዳዋ ደግሞ እስከ 300 የሚሆኑ ሰዎች መታሰራቸውን ለማወቅ ችያለሁ ያለው ኢሰመኮ የታሰሩ ሰዎችን ብዛት በሚመለከት የተሟላ መረጃ ለማግኘት አለመቻሉን ነው የገለጸው።
“በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሂደት አሁንም የቀጠለ በመሆኑ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸው ይገመታል”ም ብሏል።
አብዛኛዎቹ በጥቆማ መታሰራቸውንና ከታሳሪዎቹ የትግራይ ተወላጆች እንደሚበዙ ለማወቅ እንደተቻለም ነው የገለጸው፡፡
ሰዎች በብሔራቸው ሳይሆን በአዋጁ መሰረት ተጠርጥረው የሚያዙ መሆኑንና በሽብርተኝነት የተፈረጁት ድርጅቶች ብሔር ተኮር በመሆናቸው የሚያዙ ሰዎች የአንድ ብሔር አባላት ሊመስሉ መቻላቸው ከሕግ አስከባሪ አካላት ተገልጾልኛልም ብሏል፤ የድርጅቶቹን ብሔር ተኮርነት መገንዘቡን በመጠቆም፡፡
አንዳንዶቹ ጣቢያዎች እና የማቆያ ስፍራዎች በጣም የተጣበቡ፣ በቂ መጸዳጃ የሌላቸው እና በቂ አየር እና ብርሃን የማያገኙ እንደሆኑና ለኮሮና ወረርሽኝ ተገቢው ትኩረት አለመሰጠቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም አዋጁ መርሆዎችን ባከበረ መልኩ እየተተገበረ አይደለም ያለው ኮሚሽኑ መረጃ ያልተገኘባቸው፣ የሚያጠቡ እናቶች፣ አረጋውያን እና የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ፣ አዋጁ ከመድልዎ ነፃ በሆነ መልኩ እንዲከናወን፣ ሰብአዊ አያያዙ እንዲሻሻል እና ለክትትል ተግባራቱ ተገቢው ትብብር እንዲደረግ አሳስቧል።
በጥርጣሬ ታስረዋል የተባሉ የኢትዮጵያ ሰራተኞቹ ለፍርድ አለመቅረባቸውን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በአስቸኳይ ይፈቱ ሲል አሳስቧል፡፡
የታሰሩበት ምክንያት በውል አለመገለጹን ያስታወቁት የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የድርጅቱ ያለመከሰስ መብት እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡
እስሩ ብሔር ተኮር አለመሆኑን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እንዲናገሩና መብቶች እንዲከበሩ እንዲሁም ተኩስ ቆሞ ሁሉን ያካተተ ውይይት እንዲደረግም ጉቴሬዝ አሳስበዋል፡፡
ከሰሞኑ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ታሰሩ ስለተባሉት የድርጅቱ ሰራተኞች ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “የተመድ አሊያም የሌላ ተቋም ሰራተኛ በመሆኑ የታሰረ” አለመኖሩን ጠቁመው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ የትኛውም አካል የሀገሪቱን ሕግ አክብሮና ጠብቆ ሊሰራ እንደሚገባ ይህንን ካላደረገ ግን በሕግ እንደሚጠየቅ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡