በሶማሌና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቦታ በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 6 ሰዎች መገደላቸወን ኢሰመኮ ገለጸ
ግጭቱ የተከሰተው መሰከረም 7፣2016ዓ.ም በባቢሌ አቅራቢያ መሆኑን ኢሰመኮ ጠቅሷል
ኢሰመኮ ቀደም ሲል ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች የጥቃት ሰለባ መሆናቸው አሳሳቢ ነው ብሏል
በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቦታ በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 6 ሰዎች መገደላቸወን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
በሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት ማለፉን ባወጣው ሪፖርት አመላክቷል።
ግጭቱ የተከሰተው መሰከረም 7፣2016ዓ.ም በባቢሌ አቅራቢያ መሆኑን ኢሰመኮ ጠቅሷል።
ኢሰመኮ እንደገለጸው በሁለቱ ክልሎች መካከል በነበረው የተኩስ ልውውጥ በአካባቢው የነበሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
አሁን ላይ ግጭቱ መቆሙን የጠቀሰው ኢሰመኮ "በተኩስ ልውውጡ ወቅት ቆሎጂ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ቢያንስ ስድስት ተፈናቃዮች ተገድለዋል፣ በርካታ ሰዎች ቆስለዋል እንዲሁም በሌሎች የአካባቢው ሲቪል ሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል" ብሏል።
ኢሰመኮ ሀለቱም ክልሎች ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና የነዋሪዎችን እና የተፈናቃዮችን ደህንነት በዘላቂነት እንዲጠብቁ፣ እንዲሁም ጉዳት ያደረሱ የጸጥታ ኃይሎች ተጠያቂ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
ኢሰመኮ ቀደም ሲል ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች የጥቃት ሰለባ መሆናቸው አሳሳቢ ነው ብሏል።