ቪዲዮው የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ”ኦነግ ሽኔ” በተባሉ ሰዎች ላይ ጅምላ ግድያ ሲፈጽሙ ያሳያል - ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም
ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ የተሟላ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አሳስቧል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ፤ በትናንትነው እለት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ሲዘዋወር የነበረው በርካታ ግለሰቦች ከመኪና እየወረዱ ሲደበደቡና በጅምላ ሲገደሉ የሚያሳየው ቪዲዮ "ኦነግ ሸኔ" በተባሉ ሰዎች ላይ የተፈጸመ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመው በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ ልዩ ቦታው እንቶሊ በሚባል ስፍራ በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም የተፈጸመደ መሆኑም ኢሰመኮ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
የጅምላ ግድያው የተፈጸመው " በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ’’ ነውም ብሏል። ኢሰመኮ ይህን ይበል እንጅ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም፡፡
ኢሰመኮ፡ "ከህግ ውጭ የተፈጸመ ወንጀል" ሲል የገለጸው የጅምላ ግድያ ፤ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ባወጣው “በኢትዮጵያ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች እና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ ምርመራ” በሚል መጋቢት 2፣ 2014 ዓ.ም ያወጣው ሪፖርት ከተካተቱ ከህግ ውጭ የተፈጸመ የግድያ ድርጊት ክስተቶች አንዱ መሆኑም አስታውሷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተሟላ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነትም እንዲረጋገጥ በድጋሚ አሳስቧል።
በዚሁ ሪፖርት ላይ ኢሰመኮ ከምስክሮች እና በስፍራው በመገኘት በመስክ ምልከታ ያሰባሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግ ድርጊቱ የተፈጸመበትን ስፍራ ጠቅሶ ወቅቱም በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት ቀኑ በትክክል ያልታወቀ መሆኑንም አስፍሯል።
የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በሁለት የጭነት መኪኖች ያመጡዋቸውን እና ወደ 30 የሚጠጉ የ”ኦነግ ሸኔ አባላት” ናቸው ያሏቸውን ሰዎች በጅምላ በጥይት ደብድበው መግደላቸውን ገልጿል።
ኢሰመኮ ቪዲዮውን ላይ ተጨማሪ ማጣራትና የቴክኒክ ምርመራ ካደረገ በኋላ ከዚህ ቀደም በመስክ ምርመራ በለየው ስፍራና በቪዲዮው ላይ ያለውን ስፍራ ማነጻጸሩን አስታውቋል።
ምስሉ የተቀረጸበት ቦታ ለማነጻጸርና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የቴክኒክ ምርመራዎችን ማድረጉን ገልጾ ቪዲዮው ላይ ያለው ከፍርድ ውጭ የተፈጸመው የጅምላ ግድያ ከዚህ ቀደም ኢሰመኮ በሪፖርቱ ያካተተው ስለመሆኑ በአሳማኝ ደረጃ ማስረጃ ማግኘቱንና ማረጋገጡን አስታውቋል።