አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ 1 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ዕርዳታ መስጠቷን አስታወቀች
ሩሲያ ምእራባዊያን የውክልና ጦርነት ከፍተዉብኛል የሚል ክስ እያቀረበች ነዉ
አሜሪካ ቀደም ሲል ለዩክሬን 40 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጓ ይታወሳል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ረቡዕ እንደተናገሩት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር መሰረት ፀረ-መርከቦች ፣መድፍ ሮኬቶች እና የሃውትዘር መሳሪያዎችን ጨምሮ 1 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ወታደራዊ ድጋፍ ለዩክሬን ሰጥታለች።
ፕሬዝዴንት ባይደን ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ለመድፍ፣ ለድንበር መከላከያ እና ለዘመናዊ ሮኬት የሚውል ወጭን ጨምሮ በጥቅሉ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን አሰታዉቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ባይደን በዩክሬን ውሰጥ ያሉ ሰዎች የመጠጥ ውሃ፣ ወሳኝ የህክምና አገለግሎት፣ምግብ፣ መጠለያ እንዲያገኙ እና ቤተሰቦች አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች እንዲገዙ ለማስቻል የ225 ሚሊዮን ዶላር የሰብአዊ አርዳታ ማድረጋቸዉን አስታዉቀዋል።
አሜሪካ ያደረገችውን ወታደራዊ ድጋፍ ያደነቁት ፕሬዘደንት ዘለንስኪ እርዳታው በተለይም በሩሲያ ጥቃት ስር ያለውን የዶምባስ ግዛት ለመከላከል ይጠቅማል ብለዋል
በተመድ የሩሲያ አምቤሳደር ቫሲሊ ናቤንዚያ ምአራባውያን በሩሲያ ላይ የውክልና ጦርነት ከፍተዋል የሚል ክስ አሰምተዋል።
አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ሀገራት ሩሲያ ያዳክማል ብለው ያሰቡትን ሁሉ ማእቀብ ጥለዋል፤እየጣሉም ይገኛሉ፡፡
ሩሲያ ወዳጅ አይደሉም ያለቻቸው ምእራባውያን ሀገራት ነዳጇን በሩብል እንዲገዙ በማድረግ የተጣለባትን ማእቀብ ለመበቀል ሞክራለች፤ በዚህም የተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ፍላጎት ነጃጅ እየገዙ ነው፡፡
የአውሮፓ ህብረትም የነዳጅ ገዥ ኩባንያዎች በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማእቀብ በማይጻረር ምልኩ ነዳጅ በሩብል ምዛት ይችላሉ ማለቱም ይታወሳል፡፡
ጦርነቱ አሁንም በመካሄድ ላይ ሲሆን ሩሲያ የዶምባስ ግዛት ነጻ እስከሚወጣ ድረስ ይቀጥላል ብላለች፡፡