እንግሊዝ በሩሲያ ጦር የተማረኩ ዜጎቿን ለማዳን ማንኛውንም ነገር እንደምታደርግ ገለጸች
የወታደሮቹ ቤተሰቦች የሩሲያ መንግስት ምህረት እንዲያደርግላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ዛሬ 120 ቀናት ሆኖታል
እንግሊዝ በሩሲያ ጦር የተማረኩ ዜጎቿን ለማዳን ማንኛውንም ነገር እንደምታደርግ ገለጸች፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነበር ከሩሲያ ጋር ወደ ይፋዊ ጦርነት የገቡት፡፡
ይህ ጦርነት ከተጀመረ አራት ወር ሊሞላው 10 ቀናት ብቻ የቀሩት ሲሆን እስካሁን ድረስ ከ7 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል፡፡
እንደ ተመድ ሪፖርት ከሆነ በጦርነቱ እስካሁን ከአምስት ሺህ በላይ ዜጎች ሲገደሉ በርካቶች አካላዊ ጉዳት እንዲሁም ከፍተኛ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡
በዚህ ጦርነት ላይ የበርካታ ሀገራት ዜጎች ከዩክሬን ጎን ተሰልፈው በመዋጋት ላይ ሲሆኑ ሁለት የእንግሊዝ እና አንድ ሞሮኳዊ ዜግነት ያላቸው ሶስት ሰዎች በሩሲያ ጦር ተማርከው በዶንባስ ራስ ገዝ ግዛት ባለው ፍርድ ቤት ቀርበው የሞት ፍርድ እንደተፈረደባው ሮይርስ ዘግቧል፡፡
ዜጎቿ የታሰሩባት እንግሊዝም ምርኮኛ ወታደሮቹ ላይ የተበየነው የሞት ፍርድ እንዳይተገበር ማንኛውንም ነገር እንደምታደርግ የሀገሪቱ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ሊዝ ትሩስ ለቢቢሲ እንዳሉት አይደን አስሊን እና ሻውን ፒነር የተሰኙ የእንግሊዝ ወታደሮች በሩሲያ ጦር ለዩክሬን እየተዋጉ እያሉ ተማርከዋል ብለዋል፡፡
ከሁለቱ እንግሊዛዊያን በተጨማሪ ሳዱን ብራሂም የተሰኘ የሞሮኮ ዜግነት ያለው ወጣት በሩሲያ ጦር ተማርኮ ቅጥረኛ ወታደር ነህ በሚል የሞት ፍርድ ተላልፎበታል፡፡
ይሄንን ተከትሎም በእነዚህ ዜጎች ላይ የተወሰነው የሞት ፍርድ እንዳይተገበር መንግስት የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ማኒስትሩ አክለዋል፡፡
የክሪምሊን ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው እስካሁን ከእንግሊዝ መንግስት የቀረበላቸው ጥያቄ አለመኖሩን ገልጸው ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡