የመጀመሪያ እና ከፍተኛ ደረጃ ፍ/ቤቶች መስከረም አበራ በዋስ እንድትለቀቅ የወሰኑትን ውሳኔ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አጽንቷል
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መስከረም አበራ በ 30 ሺ ብር ዋስ እንድትለቀቅ ቢወስንም ፖሊስ ይግባኝ ጠይቆ ነበር፡፡
ይህንን ይግባኝ የተመለከተው ከፍተኛው ፍ/ቤት፤ የታችኛው ፍርድ ቤት መስከረም አበራ በ 30 ሺ ብር ዋስ ከእስር እንድትወጣ የወሰነውን ውሳኔ በማጽናት የዋስትና መብቷ እንዲጠበቅ ወስኖ ነበር።
ይሁንና ፖሊስ በድጋሚ ይግባኝ በማለቱ ጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ ሰጥቷል።
ጠቅላይ ፍ/ቤት የፖሊስን ይግባኝ ወድቅ በማድረግ መስከረም አበራ በ 30 ሺ ብር ዋስትና እንድትወጣ መወሰኑን ጠበቆቿ ሄኖክ አክሊሉ እና ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል።
መምህርት መስከረም አበራ “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዮቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት ናት፡፡
የቀድሞው አማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ የዘመቻ መምሪያ ም/አዛዥ የነበሩት ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታሁን ዛሬ ከእስር መለቀቀቃቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ቢሰጥ ለአንድ ወር ያህል በእስር ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በጋዜጠኞች እና በማህበረሰብ አንቂዎች ላይ እያካሄደ ያለው እስር ትችት አስከትሎበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ)ም የመንግስት የእስር ድርጊት ኮንኗል፡፡
ነገርግን የኢትዮጵያ መንግስት ተችዎችን እያሰራ አለመሆኑን እና እየሰራ ያለው ስራ የህግ የማስከበር ተግባር መሆኑን በተጋጋሚ እየገለጸ ይገኛል፡፡