የአሜሪካ ማዕቀብ ሰለባ የሆኑት ኢራን እና ቬንዙዌላ የ20 ዓመት ስምምነት ተፈራረሙ
በዓለም በነዳጅ ምርት ሃብታም የሆኑት ሁለቱ ሀገራት በነዳጅ ቴክኖሎጂ እና መሰረተ ልማት ላይ በጋር እንሰራለን ብለዋል
የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ቴህራንን ጎብኝተዋል
የአሜሪካ ማዕቀብ ሰለባ የሆኑት ኢራን እና ቬንዙዌላ የ20 ዓመት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
የላቲን አሜሪካዋ ቬንዙዌላ እና የመካከለኛው ምስራቋ ኢራን በዓለማችን ካሉ የነዳጅ ሀብታም ሀገራት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ሁለቱም ሀገራት በየጊዜው ከዓለማችን ልዕለ ሀያሏ አሜሪካ ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ሀብታቸውን በሚፈልጉት መንገድ በዓለም ገበያ እንዳይሸጡ ተደጋጋሚ ማዕቀቦች ተጥሎባዋል፡፡
የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ወደ ቴህራን ተጉዘው ኢራንን የጎበኙ ሲሆን ለቀጣዩቹ 20 ዓመታት የሚዘልቅ የወዳጅነት እና ትብብር ስምምነት ከኢራን አቻቸው ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ሬሲ ጋር ተፈራርመዋል፡፡
በሰሜናዊ ቴህራን ባለው ሳዳብድ ቤተመንግስት በተፈረመው በዚህ ስምምነት መሰረት ሁለቱ ሀገራት የነዳጅ ሀብታቸውን በሚገባ መጠቀም የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ እና መሰረተ ልማት ግንባታዎችን ማካሄድ ይችላሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት በመከላከያ መረጃ ልውውጥ፣ በግብርና ማዘመን፣ቱሪዝም፣ እና ሌሎች የትብብር መስኮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቬንዙዌላ አሁን እየተጠቀመችባቸው ያሉ የነዳጅ ማጣሪያ ቴክኖሎጂዎች ኋላ ቀር መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በስምምነቱ መሰረት ከኢራን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንድታገኝ ያስችላታል ተብሏል፡፡የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ሬሲ ከስምመነቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር ቬንዙዌላ የአሜሪካን እና መሰል ሀገራትን ማዕቀብ መቋቋሟን ተናግረዋል፡፡
ኢራንም ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ እና ወዳጆቿ ማዕቀብ ሲጣልባት ቆይቷል ያሉት ፕሬዝዳንት ሬሲ ሀገራቸው ማዕቀቡን ወደ እድል መቀየሯን አክለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ማዱሮ በበኩላቸው ከኢራን ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ማጠናከር እንደሚፈልጉ ገልጸው ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ከቬንዙዌላ መዲና ካራካስ ወደ ኢራኗ ቴህራን ቀጥታ በረራ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ወደ ኢራን ከማምራታቸው በፊት በቱርክ እና በአፍሪካዊቷ አልጀሪያ ጉብኝት አድርገው ከሀገራቱ መሪዎች ጋር ገንቢ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡