በአፋር ክልል ሰመራ እና አጋቲና ካምፖች የታሰሩ የትግራይ ተወላጆች በአፋጣኝና ያለቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ኢሰመኮ ጠየቀ
ኢሰመኮ በአፋር ክልል ከ8 እስከ 9 ሺህ የትግራይ ተወላጆች ታስረው እንደሚገኙ አስታውቋል
ከታሰሩት መካከል “የአእምሮ መረበሽ ደርሶባታል በሚል በሰንሰለት አስረው ያስቀመጧት ወጣት ሴት” ጭምር ይገኙበታል ብሏል ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)በማንነታቸው ምክንያት በአፋር ክልል ሰመራና አጋቲና ካምፖች ታሰረው የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በአፋጣኝና ያለቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ጠየቀ፡፡
ኢሰመኮ ከግንቦት 15 እስከ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በአፋር ክልል በሚገኙ በሁለቱም ካምፖች የሚገኙና ወደ 9 ሺህ የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች ያሉበትን ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡
በዚህም በእስር ውስጥ ሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን በተመለከተ ከመንግስት አካላት እና አገልግሎት ሰጪዎችን እንዲሁም ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማነጋገር ክትትል ሲያደርግ መቆየቱ ኢሰመኮ አስታውቋል።
ኢሰመኮ ወደ አፋር ተጉዞ ያደረገውን ቅኝት ተከትሎ ባወጣው ሪፖርት፤ በሰመራ እና አጋቲና ካምፖች ውስጥ የሚገኙ በሺዎች ሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ “ለደህንነታቸው ጥበቃ እና በወንጀል ጥርጣሬ የሚፈለጉ ሰዎችን ለመለየት” በሚል ምክንያት ከትግራይ ክልል አዋሳኝ ከሆኑ 3 የአፋር ክልል ወረዳዎች፣ ማለትም ከአብዓላ፣ ከኮነባ እና ከበረሃሌ፣ በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም ተይዘው ወደ ካምፖቹ የተወሰዱ ናቸው ብሏል።
የአፋር ክልል የጸጥታ ኃይሎች በዞንና ወረዳ ደረጃ ካሉ ሲቪል አመራሮች ጋር በመሆን በወሰዱት እርምጃ ነው ያለው ሪፖርቱ፤ በመቀጠል የትግራይ ተወላጆችን ለይተው በመሰብሰብ ከታህሳስ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በመኪና በማጓጓዝና አሁን ወደሚገኙባቸው ካምፖቹ እንዳመጡዋቸውም አስረድቷል፡፡
ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው በመጠለያ ጣቢያዎቹ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች” ከመኖሪያቸው አካባቢ እንዲወጡና በነዚህ ቦታዎችም እስካሁንም ድረስ እንዲቆዩ የተደረጉት ከፍቃዳቸው ውጪ መሆኑን” ገልጿል፡፡
“የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከመኖሪያ ቦታቸው በማሰባሰብ ወደ እነዚህ ሁለት ካምፖች እንዲሰፍሩ አድርጓል። ከ8 እስከ 9 ሺህ የሚሆን ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ናቸው። አያያዛቸው ደግሞ በእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለበት እና በፈቃደኝነት መሰረት ያደረገ አይደለም”ም ብለዋል ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርት።
በካምፖቹ ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታና የሕክምና አገልግሎት አቅርቦት እጅግ ውስን በመሆኑና በካምፑ በተከሰተ ወረርሽኝ መሰል በሽታ ለህይወት መጥፋት ጭምር ምክንያት ሆኗል ያለው ኮሚሽኑ፤ በወሊድ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በአካባቢው ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሄዶ ለመታከም ባለመፈቀዱ ችግሩን እንዳባባሰውም አስረድቷል፡፡
ባለፉት 5 ወራት ውስጥ በሰመራ ካምፕ ብቻ በበሽታ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች፣ እንዲሁም ካምፑ ውስጥ በወሊድ ወቅት ልጅ የሞተባት እናት መኖራቸውም ኮሚሽኑ ከእስረኞቹ ለመረዳት ችያለሁ ብሏል፡፡
ከታሰሩት የትግራይ ተወላጆች መካከል “ቤተሰቦቿ የአእምሮ መረበሽ ደርሶባታል በሚል በሰንሰለት አስረው ያስቀመጧት ወጣት ሴት፣ እስከ 10 የሚደርሱ ከባድ ቁስል ያለባቸው ሰዎች፣ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው 5 ሕፃናት እንዲሁም የቆዳ በሽታ ወረርሽኝ ነው በተባለ በሽታ የተጠቁ ከ4 እስከ 5 ዓመት ዕድሜ መካከል የሚገኙ ህፃናት እንደሚገኙባቸውም ኮሚሽኑ ባወታው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ መንግስት አካላት “የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለው ለሰዎቹ ደህንነት ጥበቃ እና ከጸጥታ ስጋት ጋር በወንጀል ጥርጣሬ የሚፈለጉ ሰዎችን የመለየት ስራ መስራት በማስፈለጉ” መሆኑን በሪፖርቱ አስታውቋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሰመራና አጋቲና ካምፕ ውስጥ ተይዘው የሚገኙት ሰዎች ሁኔታ በመጠለያ ጣቢያ ስም የተፈጸመ፣ በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ ሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እስር በመሆኑ በአፋጣኝ ሊለቀቁ ይገባል”ብለዋል፡፡
ዶ/ር ዳንኤል አክለውም “በፈቃዳቸው ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ለመመለስ ወይም አሁን ባሉበት ቦታ ለመቆየት ወይም ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ አስፈላጊው ድጋፍና እርዳታ ሊሰጣቸውም እንደሚገባ አሳስበዋል።
በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ካሉ በመደበኛው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ስርዓት መታየት አለበት ያሉት ኮሚሽነሩ በካምፕ የሚገኙት ሰዎች ያቅድመ ሁኔቴ በአፋጣኝ ሊለቁ ይገባል ብለዋል።