ኢሰመኮ ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙ የኦነግ አባላት በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ጠየቀ
ሌሎች የቅድመ-ክስ ታሳሪዎችም ተዓማኒ ክስ ካልቀረበባቸው በአፋጣኝ እንዲለቀቁም ጥሪ አቅርቧል
የተራዘመ ቅድመ ክስ እስር ሰዎች በፍትሕ አስተዳደር ላይ ያላቸውን እምነት እንደሚያጠፋም ገልጿል
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች ለተራዘመ ጊዜ ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረው የሚገኙ በመሆኑ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) አመራሮቹ ከእስር ከመለቀቅም ባለፈ ለደረሰባችው ጉዳት ሊካሱ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የፍርድ ቤትና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ እየተጣሰ፣ እስረኞቹ ከሕግ ውጪ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸው ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም መሆኑንም ነው ኮሚሽሩ የገለጹት፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አፋጣኝ ማጣራት አካሂዶ ተገቢውን እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባም ኮሚሽነሩ ማሳሰባቸውን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢሰመኮ በተለያዩ ፖሊስ መምሪያዎች በእስር ላይ ያሉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባሎች የእስር ሁኔታን በተመለከተ ክትትል ማድረጉን ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ፤ ከመጋቢት 1 እስከ 10 ቀን 2014 ዓ.ም በቡራዩ ፣ በገላንና በሰበታ ፖሊስ መምሪያዎች በመሄድ እስረኞችን፣ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎችን፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንን እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተወካዮችን በማነጋገር ምርመራ መደረጉንም አስታውቋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት እስረኞቹን በሚመለከት በፍርድ ቤት እና በዐቃቤ ሕግ የተሰጡ ውሳኔዎችን እና ትዕዛዞችን እንዲሁም የሕክምና ሰነዶችን መመልከቱንም ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ፤ በቡራዩ ፖሊስ መምሪያ በእስር ላይ የነበሩ አቶ ሚካኤል ጎበና፣ አቶ ኬኔሳ አያና፣ ዶ/ር ገዳ ወልጅራ፣ አቶ ዳዊት አብደታ፣ አቶ ለሚ ቤኛ፣ አቶ ገዳ ገቢሳ የተባሉ የፓርቲውን አመራሮች ማነጋሩን ጠቅሷል፡፡ ከዚህ ባለፈም የኦነግ አመራሮች የሆኑት ኮሎኔል ገመቹ አያና በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል፣አቶ አብዲ ረጋሳ ደግሞ ገላን ከተማ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ካምፕ ውስጥ በእስር ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ከቤተሰቦቻችና ከጠበቆቻቸው መረጃ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ አቶ በቴ ኡርጌሳ በእስር ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት በፖሊስ ዋስትና ተፈቅዶላቸው በአንድ የሕክምና ተቋም ሕክምና ላይ የነበሩ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
የኢሰመኮ የሲቪል፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ጂብሪል (ዶ/ር)፤ ታሳሪዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመሆናቸው በሕዝባዊ አገልግሎት ስራቸው ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይጋለጡ ጥበቃ ሊደረግ ሲገባ፤ በተግባር የተገላቢጦሽ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ አፋጣኝ እልባት እንደሚስፈልገው ኮሚሽነር አብዲ ጂብሪል (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡