በነገው ጨዋታ ጠንካራውን ማንችስተር ዩናይትድ ትመለከታላችሁ - ሩብን አሞሪም
ነገ ምሽት 12 ሰዓት በኤፍኤ ካፕ ፍልሚያ ከአርሰናል ጋር የሚገናኘው ዩናይትድ ዋንጫውን እንዲያነሳ እንደሚፈልጉ አሰልጣኙ ተናግረዋል
ባለፈው ሳምንት በፕሪምየር ሊግ ከሊቨርፑል ጋር በሰፊ ውጤት ልዩነት እንደሚሸነፉ ሲጠበቁ በአቻ ውጤት ያጠናቀቁት ቀያይ ሰይጣኖቹ በጥሩ መነቃቃት ላይ እንደሆኑ እየተነገረ ነው
ማቸስተር ዩናይትድ በነገው ዕለት ምሽት 12 ሰዓት በሶስተኛው ዙር የኤፍኤ ካፕ ፍልሚያ ከአርሰናል ጋር የሚገጥም ይሆናል፡፡
የቀያይ ሰይጣኖቹ አለቃ ሩበን አሞሪም ቡድናቸው በውድድሩ እንዲዘልቅ እና በግንቦት ወር ዋንጫውን እንዲያነሳ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በሊቨርፑል ጨዋታ ላይ በቡድኑ ላይ የታየውን ተጋድሎ እና መነቃቃት በማስቀጠል በነገው ጨዋታ ጠንካራውን የማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን ይዞ ለመቅረብ ቃል ገብተዋል፡፡
ባለፈው ወር በኤሜሬትስ ከአርሰናል ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ባደረጉት ጨዋታ ለተከታታይ ሶስት ጊዜ በመድፈኞቹ በመሸነፍ መጥፎ ታሪክ የጻፉት ቀያይ ሰይጣኖቹ፤ በነገው ዕለት ለበቀል ወደ ሜዳ ይገባሉ ሲል የእንግሊዙ ሚረር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ ከመድፈኞች ጋር ካደረጉት ጨዋታ በኋላ በጉዳት ላይ የነበሩ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች መመለስ የቡድኑን ስብስብ እንደሚያጠናክረውም ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከሊቨርፑሉ ጨዋታ በኋላ ምንም ጨዋታ ያላደረጉት ዩናይትዶች ሰፊ የመዘጋጃ ጊዜ ማግኘታቸው ለቡድኑ ተጨማሪ አቅም ይሰጠዋል ተብሏል፡፡
አሞሪም ከጨዋታው በፊት በሰጡት አስተያየት “ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ አዳዲስ እግሮችን መምረጥ ቢኖርብኝም አሁን ላይ ተጨዋቾቼ በተመሳሳይ መነሳሳት እና አቋም ላይ እንዳሉ ይሰማኛል፤ በነገው ጨወታም ከአንፊልዱ ፍልሚያ ብዙ የተማረ የተሻለ ጠንካራ ቡድን ይዘን እንቀርባለን” ብለዋል፡፡
ዩናይትድ ባለፈው የውድድር ዘመን 13ኛውን የኤፍኤ ዋንጫን ማሸነፍ ችሏል። ባለፉት 40 አመታት ደግሞ በሶስተኛው ዙር ከውድድሩ የተሰናበተው 3 ጊዜ ብቻ ነው። አርሰናል በበኩሉ የውድድሩን 14 ዋንጫዎች አንስቷል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከሊጉ መሪ በ6 ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል በበኩሉ በባለፈው በካራባኦ ካፕ በኒውካስትል 2-0 ተሸንፏል፡፡
የቡድኑ ዋነኛ ሰው ቡካዮ ሳካ ባደረገው አነስተኛ ቀዶ ጥገና ምክያንት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ ተነግሯል፡፡
ታዳጊው ኢታን ንዋኔሪ በጉዳት ሳካን ተቀላቅሏል፤ ታኬሂሮ ቶሚያሱ እና ቤን ኋይት በተመሳሳይ ከነገው ጨዋታ ውጭ እንደሚሆኑ ተዘግቧል፡፡
ሊያንድሮ ትሮሳርድ የሳካን ቦታ እንደሚተካ ይጠበቃል። ራሂም ስተርሊንግ ከጉዳት ተነስቶ በመጨረሻው ጨዋታ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ነበር ፤ ማርቲን ኦዴጋርድ ከዲላን ራይስ ጋር እንደሚጣመሩ ይጠበቃል፡፡