በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተፈጸመው “አሰቃቂ ግድያ” ላይ የመንግሥት ፀጥታ አካላት መሳተፋቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
ለድርጊቱ መነሻ የሆነው በ20 የፀጥታ አባላት እና በሲቪል ሰዎች በታጣቂዎች የተፈጸመ ግድያ ነው ተብሏል
በግድያው የተጠረጠረ ግለሰብ “በአካባቢው በተፈጸመው ጥቃት ላይ እጃችን አለበት፤ ባምዛ በሚባለውና በግልገል በለስ ቦታዎች ሰዎች አሉን” ማለቱ ተገልጿል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጸመውን “አሰቃቂ ግድያ” ላይ የመንግሥት ፀጥታ አካላት መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ኮሚሽኑ እንዳለው ክስተቱ የተፈጸመው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ ነው።
ይህ ድርጊት የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም መፈጸሙንም ኮሚሽኑ ገልጿል። ኢሰመኮ ፤ መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችና በርካታ ተመልካቾች በተሰበሰቡበት አስክሬኖች እና አንድ በሕይወት የነበረ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ እሳት ውስጥ ሲጨመር የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ እንደነበርና ይህንንም ሁኔታ ማጣራቱን ገልጿል።
ኢሰመኮ፤ ምስክሮችን በማነጋገር እንዳጣራና ክስተቱ የተፈጸመው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ ውስጥ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም መሆኑን አረጋግጧል።
“ከዳኝነት ውጪ የተፈጸመ ግድያ” እና አስክሬኖችንና አንድ በሕይወት የነበረ ሰው ጭምር የማቃጠል ድርጊቱ የተፈጸመው በመንግሥት የፀጥታ አባላትና ሌሎችም ሰዎች ተሳትፎ ጭምር እንደሆነ አረጋግጫለሁ ብሏል።
ለዚህ ክስተት መነሻ የሆነው በ20 የመንግሥት ፀጥታ አባላት እና በሲቪል ሰዎች ላይ በታጣቂዎች ከአንድ ቀን በፊት የተፈጸመው ግድያ እንደሆነም ተገልጿል።
የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በመተከል ዞን፣ በጉባ ወረዳ፣ አይሲድ ቀበሌ፣ አፍሪካ እርሻ ልማት ማኅበር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከቀኑ 8 ሰዓት ሰዓት ገደማ፣ ከግልገል በለስ ከተማ በመኪና ተሳፍረው፣ በአካባቢው ካለው የደኅንነት ስጋት አንጻር በተለመደው አሰራር መሰረት በመከላከያ ሠራዊት ታጅበው ወደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ፤ ወደ ማንኩሽና ወደ አሶሳ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ ሰዎች ላይ ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ፈጽመው እንደነበር ኢሰመኮ አስታውቋል።
በዚህ ጥቃትም አንድ አሽከርካሪ፣ አንድ በንግድ ሥራ የሚተዳደር ሰው እና አንድ መምህር በአጠቃላይ ሶስት ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ ኮሚሽኑ ማጣራቱን ገልጿል።
መንገደኞቹን አጅበው በመጓዝ ላይ የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ያሉበት መኪና በከባድ መሳሪያ ተመትቶ ሻለቃ አመራሩን ጨምሮ ቢያንስ 20 የመከላከያ ሠራዊት አባላት መገደላቸውን፤ በ14 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱንም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።
በዚህ ዕለትም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና እና ጥቃቱን በፈጸሙ የታጠቁ ኃይሎች መካከል የተደረገው ውጊያ ከቀኑ 8 ሰዓት እስከ ረፋዱ 12 ሰዓት ቆይቶ ነበር ተብሏል።
በማግስቱ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ተጨማሪ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በቦታው ደርሰው ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ድረስ በቆየ የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ ከታጣቂዎቹ መካከል ወደ 30 የሚሆኑ መገደላቸውንና ቀሪዎቹ ታጣቂዎች መሸሻቸውን ኢሰመኮ ማረጋጡን አስታውቋል።
ይህን ተከትሎም የመንግሥት ፀጥታ አካትና የሲቪል ሰዎች መንገደኞች መኪኖች የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት አይሲድ ከተማ መድረሳቸው ተገልጿል።
የመንግሥት የፀጥታ አባላቱ “አግኝተናል” ባሉት ጥቆማዎች መሰረት በአካባቢው በነበሩ ተሽከርካሪዎችና በመኖሪያ ቤቶች ላይ እንዲሁም ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ማንኩሽና ባምዛ ይጓዙ የነበሩ ሲቪል ሰዎች ላይ ፍተሻ ማካሄድ እንደተጀመረ ተገልጿል።
በፍተሻው ሂደት ውስጥ የጸጥታ አካላት በቅርቡ ከእስር ተፈትተው ከመተከል ዞን ማረሚያ ቤት የይለፍ ወረቀት በመያዝ ወደ መኖሪያቸው የተመለሱና የአካባቢው ነዋሪዎች የነበሩ 8 የትግራይ ተወላጆችን “እናንተ ናችሁ መረጃ ሰጥታችሁ ጥቃቱን ያስፈጸማችሁት” በማለት ከተሳፈሩበት መኪና አስወርደዋቸዋል ተብሏል።
በተደረገው ፍተሸም አንድ የወታደራዊ መገናኛ ሬዲዮ፣ የተለያዩ ፎቶግራፎች እና ከ40 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ እንደተገኘ ሲሆን፤ የመንግሥት ፀጥታ አባላትም ተጠርጣሪዎቹን እየደበደቡ ተጨማሪ መረጃ መጠየቅ መጀመራቸው ተገልጿል።
ይህንን ተከትሎም ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ “በአካባቢው በተፈጸመው ጥቃት ላይ እጃችን አለበት፤ ባምዛ በሚባለውና በግልገል በለስ ቦታዎች ሰዎች አሉን” ማለቱን ተከትሎ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላቱ ሁኔታውን የተቃወሙ ሁለት የጉሙዝ ተወላጆችን ጨምሮ 10 ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውን ኢሰመኮ አስውቋል።
ከዚህ በመቀጠልም የፀጥታ ኃይል አባላት የተገደሉትን ሰዎች አስከሬኖች ከከተማዋ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ ጫካ ስፍራ በመውሰድ አስክሬናቸውን ማቃጠል መጀመራቸውን የዓይን ምስክሮች ማስረዳታቸውን ኮሚሽ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በዚህ መካከልም ከተጠርጣሪዎቹ ተገዳዮች ጋር ግንኙነት አለው የተባለን አንድ ሌላ የትግራይ ተወላጅ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተሳፈረበት መኪና ውስጥ ተደብቆ በጥቆማ ካገኙት በኋላ በገመድ አስረው በመውሰድ ቀድሞ በመቃጠል ላይ ከነበሩት አስክሬኖች ላይ እንደጨመሩት እና በእሳት ተቃጥሎ እንደሞተ ምስክሮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል ነው የተባለው።
በአካባቢው የነበሩት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላትና የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት ሲሆኑ፤ በአጠቃላይ ሁኔታው በቀጥታ ድርጊት በመፈጸም ወይም አስገዳጅ ተግባሮችን ባለመፈጸም የነበራቸው የተለያየ የተሳትፎ መጠን በተጨማሪ የወንጀል ምርመራ ሊጣራ የሚገባው እንደሆነ የኮሚሽ መግለጫ ያመለክታል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፤ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እጅግ ፈታኝ በሆኑ አካባቢዎች በከፍተኛ መስዋዕትነት የሕዝብ ደኅንነት የሚጠብቁ መሆኑ የማይዘነጋ ሕዝባዊ አገልግሎት ነው ብለዋል።
ይህ ቢሆንም ግን በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ከዳኝነት ሂደት ውጭ መግደል እና በተለይም በእሳት አቃጥሎ መግደል ፈጽሞ ከሕግ አስከባሪ አባሎች የማይጠበቅ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመሆኑ የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተጠርጣሪዎች ላይ ተገቢውን የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ እንዲደረግ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አክለውም “የመንግሥት ሕግ አስከባሪ አባሎች እራሳቸው በግልጽ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎች ሆነው መታየታቸው፤ ሰዎች በሕጋዊ ሥርዓት ላይ የሚኖራቸውን እምነት የሚሸረሽርና ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚያጋልጥ ነው ብለዋል።
መንግሥት የምርመራውን ሂደትና ውጤት በተመለከተ የተሟላ መረጃ ለሕዝብ ይፋ ሊያደርግና ፍትሕን ለማረጋገጥም የሟች ቤተሰቦችን ሊክስ ይገባል”ም ብለዋል።
መንግስት፤ ንፁሃንን በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ሲያደርጉ በታዩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ትናንትና መግለጹ ይታወሳል።