"ተበድሎ ይቅር ያለን ሰው አሏህ የሠራውን ጥፋት ይቅር የሚለው በመኾኑ ሁላችንም ይቅር ልንባባል ይገባል"- ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ
የ1445ኛው የዒድ አል-አድኃ (አረፋ) በአል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘነድ በነገው እለት በመላው አለም ይከበራል
ሁሉም የሰላም ዘብ እንዲሆን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሐጂ ኢብራሒም ጥሪ አቅርበዋል
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የ1445ኛውን የዒድ አል-አድኃ (አረፋ) በዓል ሲያከብር ካለው ላይ ለአቅመ-ደካማ ወገኖቹ እንዲያካፍል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሼክ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ አሳሰቡ።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት፣ የዒድ አል-አድኃ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ነው።
ሸይኽ ሐጂ በዚሁ መልዕክታቸው፣ በዙልሒጃ ወር የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት የሚሰሩ መልካም ተግባራት አሏህ ዘንድ በሌሎች ቀናት ከሚሰሩ መልካም ተግባራት በላጭ ምንዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በሙስሊሙ ማኅበረሰብ በጉጉት ከሚጠበቁት የዙልሒጃ ወር የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት ዘጠነኛዋ ቀን አል ሐጁል አረፋ የሚደረግበትና ማግሥቱ ቀን (የውመል ነሀር) የአረፋ በዓል የሚከበርበት መሆኑን ፕሬዚደንቱ አውስተዋል።
አረፋ ሙስሊሞች የዑድሂያ እርድ የሚያከናውኑበት መሆኑን የጠቀሱት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፣ የእምነቱ ተከታዮች ከሚያርዱት እርድ ለተቸገሩ ወገኖቻቸው፣ በተለይም ለአቅመ ደካማና በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ችግሮች ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲያካፍሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል
"አሏህ ይቅር ባይነትን ይወዳል" ያሉት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፣ "ተበድሎ ይቅር ያለን ሰው፣ አሏህ የሠራውን ጥፋት ይቅር የሚለው በመኾኑ፣ ሁላችንም ይቅር ልንባባል ይገባል" ሲሉ ነው መልዕክት ያስተላለፉት
በበአሉ አጋጣሚውን ያገኙ የዓለም ሙስሊሞች አረፋ ላይ ሲቆሙ፣ ሌሎች ምእመናን ደግሞ በያሉበት የአረፋን ፆም በመፆም፣ ያለፉት ሁለት ዓመታት ወንጀሎቻቸው ከፈጣሪ ምህረት የሚገኝባት ቀን መሆኗን ተናግረዋል።
የዘንድሮውን ዒድ አል-አድኃ (አረፋ) የሚከበረው ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር እያደረገች በምትገኝበት ወቅት ላይ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ለጋራ ሀገራዊ ሰላም ጠቃሚ መኾኑን በመረዳት ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በያለበት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ የሚኖረውን ፋይዳ በመረዳት ጠቅላይ ምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያዎችን፣ ዓሊሞችን፣ ምሑራንን፣ ታዋቂ ግለሰቦችንና ለሀገር የሚያስቡ ሰዎችን በማሰባሰብ የሙስሊሙን ጥያቄዎች በማደራጀት ለሚመለከተው አካል መላኩን ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል።
ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው ያሉት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፣ ሁሉም የሰላም ዘብ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈው፣ ለሀገራችንና ለመላው ዓለም ሙስሊሞች በዓሉ የደስታ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።