ልዩልዩ
ግብጽ ከባቡር አደጋው ጋር በተያያዘ 8 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አዋለች
እ.ኤ.አ በ2002 በደቡባዊ ካይሮ ያጋጠመው የባቡር ላይ የእሳት አደጋ 360 ሰዎችን መግደሉ የሚታወስ ነው
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የባቡር ካፒቴኖችና ረዳቶቻቸው ይገኙበታል ተብሏል
በካይሮ ከደረሰው የባቡር አደጋ ጋር በተያያዘ 8 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የግብጽ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል 2ቱ የባቡር ካፒቴን ናቸው ያለው ዐቃቤ ህጉ የምድር ባቡር ባለስልጣናት እንደሚገኙበትም አስታውቋል፡፡
የባቡር አደጋው ባሳለፍነው አርብ የደረሰ ነው፡፡
በሁለት ባቡሮች ግጭት በደረሰው በዚህ አደጋ የ18 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ200 የሚልቁ ሰዎች ደግሞ ለተለያዩ ጉዳቶች ተዳርገዋል እንደ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሃማዳ ኤል ሳዊ መግለጫ፡፡
የግብጽ የምድር ባቡር ባለስልጣን እንዳስታወቀው አደጋው በሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ ወደ ምትገኘው አሌክሳንድሪያ ለመግባት ተቃርቦ የነበረው ባቡር የድንገተኛ ጊዜ ፍሬን በመነካቱ የደረሰ ነው፡፡
ይህ ባቡሩ ከበስተኋላው በሌላ ባቡር እንዲገጭ እና ሌሎች ሁለት መኪኖች እንዲገለበጡ ምክንያት ሆኗል፡፡
የሟቾቹ ቁጥር በመጀመሪያ 32 ነበር የተባለው፡፡ ሆኖም ባለስልጣኑ በዛሬ መግለጫው 18 መሆኑን አስታውቋል፡፡