ከ60 በሚበልጡ ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሷል
በግብፅ ሁለት ባቡሮች ተጋጭተው በትንሹ የ32 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለፀ።
የግብፅ የባቡር ትራንስፖርት ባለስልጣን ምንጮች እንዳስታወቁት፥ የባቡር አደጋው በደቡባዊ ግብፅ ሶሃግ ግዛት ታህታ ከተማ ነው የደረሰው።
አደጋውም በሁለት የመንገደኞች ባቡር መካከል በተፈጠረ ግጭት የደረስ ሲሆን፤ እስካሁንም በአደጋው የ32 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተጨማሪም ቁጥራቸው ከ60 በሚበልጡ ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት የደረሰ ሲሆን፥ ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን የማውጣት ስራው መቀጠሉም ተነግሯል።
በግብፅ በተደጋጋሚ የባቡር አደጋዎች የሚደርሱ ሲሆን፤ በአውሮፓውያኑ በ2018 በሰሜናዊ ግብፅ በደረሰ የባቡር አደጋ የ15 ሰዎች ህይወት አልፎ 40 ሰዎች ላይ ጉዳት ሲያድርስ፤ በ2019 ደግሞ በካይሮ ራምሴስ የባቡር ጣቢያ በአንድ ባቡር ላይ በተነሳ እሳት 25 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
በግብፅ የባቡር አደጋ የተለመደ ሲሆን፤ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረቱ አናሳ ነው በማለት ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ወቀሳ ያቀርባሉ።