በቴዲ አፍሮ የተዘጋቸው ዝማሬ 'የዓባይ ህብረ ዝማሬ' ይሰኛል
በታዋቂው ድምጻዊ ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ፕሮዲዩስ የተደረገና 'የዓባይ ህብረ ዝማሬ' የተሰኘ የኪነ ጥበብ ስራ በጎንደር ዩኒቨርስቲ በዛሬው እለት ተመርቋል።
ህብረ ዝማሬው በጎንደር ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀ ሲሆን ቴዲ አፍሮ በማያ ፕሮዳክሽን በኩል አዘጋጅቶታል ተብሏል፡፡
ህብረ ዝማሬው ለመጀመሪያ ጊዜ በ2013 ዓ/ም የዩኒቨርስቲው የምረቃ ስነስርዓት ላይ በገብረማርያም ይርጋ አዘጋጅነት በፋሲለደስ ባህል ቡድን ቀርቦ ነበር።
በምረቃ ስነ ስርዓቱም ላይ የቀድሞውን የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)ን ጨምሮ እውቁ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ተገኝቶ ነበር።
በስነ ስርዓቱም ዩኒቨርስቲው የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል። በዚያን ጊዜም ነበር ቴዲ ቅንብሩን በተሻለ መንገድ አሳድጎ ለመስራት ቃል የገባው።
በቃሉ መሰረትም ህብረ ዝማሬው በእውቁ አቀናባሪ አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ አቀናባሪነት ፕሮዲዩስ ተደርጎ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ/ም የመንግስት ባለስልጣናት እውቅ የኪነ ጥበብ ሰዎች እንዲሁም የዩኒቨርስቲው እና የጎንደር ከተማ አስተዳደር አካላት በተገኙበት ለመመረቅ በቅቷል።
ሆኖም ቴዲ አፍሮ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ አልተገኘም።
አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ኃያል ሀገራት ኪነ ጥበብ ትልቅ አቅም መሆኑን አውቀው ባህልና እሴቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እየሰሩም ነው ያሉት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ለግድቡ ግንባታና ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል 'ሶፍት ፓወር' ትልቅ አቅም መሆኑን በመጠቆም።
በምረቃ ስነ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።