አዲሱ አልበም "ኢትዮሪካ" የሚል መጠሪያ እንደተሰጠውም ሰዋሰው መልቲሚያ አስታውቋል
ተወዳጁ ሙዚቀኛ የክብር ዶ/ር ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) "ኢትዮሪካ" የተሰኘ ስድስተኛ አልበሙን በመጪው አዲስ ዓመት ለአድማጮች ሊያደርስ ነው ተባለ።
ድምጻዊው ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ አዲስ አልበሙን በቅርብ እንደሚለቅ የሰዋሰው መልቲሚዲያ የሙዚቃ ክፍል ኃላፊ ሀብቱ ክፍሌ ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል።
አልበሙ በሰዋሰው መተግበሪያ በኩል እንደሚወጣም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
አልበሙ እየተሰራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ሀብቱ፤ ስለ አልበሙ ይዘት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ድምጻዊው ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከሙዚቃ አሰራጩ ሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር አብሮ ለመስራት ባሳለፍነው ህዳር ወር ላይ መፈራረሙ ይታወሳል።
የክብር ዶ/ር ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የመጨረሻ አልበሙን በ2009 ዓ.ም ኢትዮጵያ በሚል ስያ አለድማጮች ማድረሱ ይታወሳል።
የግጥማ ዜማ ደራሲ ድምጻዊ አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ አቡጊዳ፣ ያስተሰርያል፣ ጥቁር ሰው እና ኢትዮጵያ የተሰኙ የሙዚቃ አልበሞቹን ከአድናቂዎች ዘንድ አድርሷል።
እንዲሁም ለኃይሌ ገብረ ሥላሴ እና ለሌላኛው የኦሊምፒክ ጀግና ቀነኒሳ በቀለ በኦሊምፒክስ ካሸነፉ በኋላ ያወጣቸው ወቅታዊ ሙዚቃዎች፣ እንዲሁም ደግሞ በአባይ በሚል ያወጣው ነጠላ ዜማ ህዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን አትርፈውለታል።
አርቲስት አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በ2022 በአፍሪማ የሙዚቃ ሽልማት ምርጥ የሬጌ ሙዚቃ ሽልማትን ማሸነፉም ይታወሳል።
አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ናዕት” በሚለው ሙዚቃው ነው የአፍሪማ ሽልማት ምርጥ የሬጌ ሙዚቃ ሽልማትንማሸነፍ የቻለው።