የጋዛው ጦርነት ባደበዘዘው የግብጽ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አልሲሲ አሸነፉ
የግብጽ ብሄራዊ የምርጫ ባለስልጣን እንዳስታወቀው፥ አልሲሲ 89 ነጥብ 6 በመቶ ድምጽ በማግኘት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን አሸንፈዋል
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ምርጫ የተመዘገበው የመራጮች ቁጥርም ታሪካዊ ነው ተብሏል
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ለቀጣዮቹ ስድስት አመታት በስልጣን መቆየት የሚያስችላቸውን ድምጽ አገኙ።
አልሲሲ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ምርጫ 89 ነጥብ 6 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ባለስልጣን ይፋ አድርጓል።
ከሶስት እምብዛም ከማይታወቁ ተፎካካሪዎች ጋር የተወዳደሩት አብዱልፈታህ አልሲሲ ማሸነፋቸው የሚጠበቅ ነበር።
ፕሬዝዳንቱ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ድምጻቸውን እንዳያሰሙ ማፈናቸውም ቀደም ብሎ ሲያስወቅሳቸው እንደነበር አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ለመሳተፍ ከተመዘገቡት 67 ሚሊየን ግብጻውያን 66 ነጥብ 8 በመቶው ድምጽ መስጠታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ይህም በግብጽ የምርጫ ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
የጋዛ ጦርነት ያደበዘዘው ምርጫ፤ የኑሮ ውድነት እና የሰብአዊ መብት አያያዝ
አልሲሲን ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ያስመረጠው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ምክንያት ትኩረት አላገኘም።
ፕሬዝዳንቱ የምርጫው ውጤት ከተገለጸ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት “ግብጻውያን ይህን ኢሰብአዊ የሆነ ጦርነት ለመቃወም ድምጻቸውን ሰጥተዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ካይሮ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ አንስቶ እስራኤል ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ለማስወጣት የምታካሂደውን ዘመቻ እንድታቆም መጠየቋንም አስታውሰዋል።
ጦርነቱ እየገፋ ሄዶ ፍልስጤማውያን ወደ ግብጽ በገፍ ከገቡ ግብጽ ከእስራኤል ጋር ወደ ጦርነት መግባቷ እንደማይቀርም ከዚህ ቀደም መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ግብጽ የባለፈውን ሳምንት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያካሄደችው በከባድ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ ሆና ነው።
የሀገሪቱ ወርሃዊ የዋጋ ግሽበት ከ30 በመቶ በላይ ደርሷል፤ ባለፉት 22 ወራትም የግብጽ ፓውንድ ከዶላር አንጻር ያለው ዋጋ በ50 በመቶ ቀንሷል።
ከ105 ሚሊየን ግብጻውያን ውስጥ ሲሶው ወይም ከ35 ሚሊየን በላዩ በድህነት ውስጥ እንደሚኖሩም መረጃዎች ያሳያሉ።
ፕሬዝዳንት አልሲሲ በሰብአዊ መብት አያያዝና የተቃውሞ ድምጽን ለማፈን በሚወስዱት እርምጃም ከምዕራባውያን የሰላ ትችት ይሰነዘርባቸዋል።
መሀመድ ሙርሲን በ2013 ገልብጠው ወደ ስልጣን የመጡት አልሲሲ በ2014 በተካሄደ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸንፈው ስልጣናቸውን አጽንተዋል።
በ2018 ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ከተመረጡ በኋላም የፕሬዝዳንቱን የስልጣን ዘመን ከአራት አመት ወደ ስድስት አመት ከፍ እንዲል ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
በቅርቡ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን አሸንፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ የኑሮ ውድነትን የመቀነስና የሚነሳባቸውን የሰብአዊ መብት አያያዝ ወቀሳ የማስተካከል ከባድ ሃላፊነት እንዳለባቸው ተንታኞች ያነሳሉ።