ፕሬዝደንት ሲሲ ቀጣናው "ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ" ሊሆን ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ
የእስራኤል ጦር ከትናንት ምሽት ጀምሮ በሰሜን ጋዛ ወረራ ፈጽሞ ይዞታውን እያሰፋ መሆኑን አስታውቋል
ፕሬዝዳንቱ ግጭቱ የሚስፋፋ ከሆነ ሁኔታው ፈንድቶ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል ብለዋል
የግብጹ ፕሬዝደንት አቡዱል ፋታህ አልሲሲ ቀጣናው "ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ" ሊሆን ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ አሰምተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ግጭቱ የሚስፋፋ ከሆነ ሁኔታው ፈንድቶ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ሲሲ ባለፈው አርብ እለት የግብጽን የአየር ክልል ጥሳ የገባችው ድሮን መያዟን ተከትሎ የሀገሪቱ ሉአዊነት መከበር አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
እስራኤል በግብጿ የቀይ ባህር ከተማ ታባ ላይ ለደረሰው የሚሳይል ጥቃት የሀማስ አጋር ናቸው ያለቻቸውን የሀውዚ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጋለች።
ሚሳይሉ ባደረሰው ፍንዳታ በታባ ሆስፒታል አካባቢ የነበሩ ስድስት ሰዎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።
ግብጽ ሚሳይሉን ማን እንደተኮሰው ባትገልጽም መነሻው ደቡብ ቀይ ባህር ነው የሚል መልስ ሰጥታለች።
እንዲህ አይነት ክስተቶች ግጭቱ ወደ ቀጣናው ይስፋፋል የሚል ስጋት ደቅነዋል።
የእስራኤል ጦር ከትናንት ምሽት ጀምሮ በሰሜን ጋዛ ወረራ ፈጽሞ ይዞታውን እያሰፋ መሆኑን አስታውቋል።
የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በትናንትናው እለት በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ በአብላጫ ድሞጽ አጽድቋል።
ነገርግን ሀማስን ከምድረ ገጽ ካላጠፋሁ አላርፍም የምትለው እስራኤል በተመድ ውሳኔ እንደማትገዛ እና ተኩስም እንደማታቆም ገልጻለች።
ሀማስ ተኩስ እንዲቆም እንደሚፈልግ እና ያገታቸውንም ሰዎች እንደሚለቅ ሲገልጽ ቆይቷል።
እስራኤል ተኩስ ለማቆም ፍቃደኛ አለመሆኗን ተከትሎ ሀማስም በሙሉ አቅሙ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
እስራኤል የሀማስ ይዞታ የሆነችውን ጋዛን መክበቧን ተከትሎ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ተዳርገዋል።