በ2030 የአለማችን አዛውንቶች ቁጥር ከወጣቶቹ ይበልጣል - ተመድ
የመንግስታቱ ድርጅት ይፋ ባደረገው ትንበያ እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሮ በ2050 1.6 ቢሊየን ይደርሳል ብሏል
“አለማቀፉ የአዛውንቶች ቀን” በየአመቱ ጥቅምት 1 ይከበራል
በአለማቀፍ ደረጃ እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ቁጥር በ2030 ከወጣቶቹ እንደሚበልጥ የመንግስታቱ ድርጅት ትንበያ አመላከተ።
የአዛውንቶች ቁጥር በአምስት አመታት ውስጥ ከአምስት አመት በታች ከሆኑ ህጻናት በእጥፍ እንደሚልቅም ይገመታል ብሏል ድርጅቱ።
የመንግስታቱ ድርጅት በፈረንጆቹ 1990 ጥቅምት 1 “አለማቀፍ የአዛውንቶች ቀን” ሆኖ እንዲከበር መወሰኑ ይታወሳል።
በእለቱም እየጨመረ የመጣውን እድሜያቸው የገፋ ሰዎች ችግሮች ለመቅረፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ይመከራል።
የመንግስታቱ ድርጅት ወጣት የሚለውን ብያኔ የሰጠው እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ያሉትን ነው።
በአዲሱ መረጃውም በ2050 እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች ቁጥር ከወጣቶቹ በእጥፍ ጨምሮ 1.6 ቢሊየን እንደሚደርስ ነው ያመላከተው። ግምቱ እውን የሚሆን ከሆነ የአዛውንቶች ቁጥር ከጠቅላላው ህዝብ 16 በመቶውን ይሸፍናል ብሏል አናዶሉ በዘገባው።
በፈረንጆቹ 1950 በአለማችን ከ20 ሰዎች ውስጥ እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑት ውክልና አንድ ብቻ ነበር (5 በመቶ)። በ2021 ይህ ምጣኔ ወደ 10 በመቶ ከፍ ብሏል። በዚሁ ከቀጠለም በ2050 ከስድስት ሰዎች ውስጥ አንዱ አዛውንት ይሆናል ይላል የተመድ ትንበያ።
እስያ እና አውሮፓ በአለማችን እድሜያቸው የገፋ በርካታ ሰዎች የሚገኙባቸው አህጉራት ናቸው።
ጃፓን ከአጠቃላይ ህዝቧ 30 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ናቸው። ጣሊያን ደግሞ በ23 በመቶ የአዛውንት ህዝብ ድርሻ ቶኮዮን ትከተላለች።
ፊንላንድ፣ ፖርቹጋል እና ግሪክ እያንዳንዳቸው ከጠቅላላ ህዝባቸው የአዛውንቶቹ ድርሻ 22 በመቶ በመሆን ከጣሊያን ይከተላሉ።
ሆንግ ኮንግ እና ደቡብ ኮሪያ እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሚሆነው ህዝባቸው ምጣኔ ከጠቅላላው እስከ 40 በመቶ በመድረስ ጃፓንን እንደሚቀድሙ የተመድ ትንበያ አመላክቷል።
በ2050 በርካታ አዛውንቶች የሚገኙት በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት ይሆናል የሚለው የመንግስታቱ ድርጅት፥ ታዳጊ ሀገራት እድሜያቸው ለገፉ ሰዎች አስቀድመው መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ እንዲጠመዱ ጥሪ አቅርቧል።
ድርጅቱ 34ኛውን “አለማቀፍ የአዛውንቶች ቀን” ሲያከብርም እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ክብራቸው ተጠብቆ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ በሚረዱ ጉዳዮች ምክክሮች ይደረጋሉ ተብሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት በትንበያው የአለም ህዝብ ቁጥር በ2030 8 ነጥብ 5 ቢሊየን፤ በ2050 9.7 ቢሊየን፤ በ2100 ደግሞ 10.4 ቢሊየን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።