አዛውንቶቹ ዘራፊዎች
ራበን ያሉ የጃፓን አዛውንቶች ተደራጅተው ወደ ዘረፋ ገብተዋል
ፖሊስ ባደረገው ብርቱ ክትትል አዛውንቶቹ ከነ ኢግዚቢቱ ተይዘዋል
አዛውንቶቹ ዘራፊዎች
በጃፓኗ ሆኬዶ በተሰኘችው የወደብ ከተማ ቤቶች እየተሰበሩ ዝርፍያ ይፈጸምባቸዋል፡፡ ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ የወንጀሎቹን ፈጻሚዎች በቀላሉ ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡
ፖሊስ ወንጀሉን ቶሎ እንዳይደርስበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ወንጀሉን አዛውንቶች ላይፈጽሙት ይችላሉ በሚል ነበር፡፡
በመጨረሻም ሁነቶችን ለመከታተል የተተከሉ ካሜራዎችን ከተመለከተ በኋላ ዝርፊያውን አንድ አዛውንት ሲፈጽም ይመለከታል፡፡
የአንዱን አዛወንት እንቅስቃሴ ለይ ባደረገው ክትትል የ88፣ 70 እና 69 ዓመት እድሜ ያላቸው ጃፓናዊያን አዛውንቶች ተደራጅተው ሲሰርቁ መቆየታቸውን ያረጋግጣል፡፡
እነዚህ አዛውንት ጃፓናዊያን አንዱ የሚሰበሩ ቤቶችን በማጥናት ሲሰብር እና ሲሰርቅ፣ አንዱ ደግሞ የተሰረቁ ንብረቶችን በማጓጓዝ ሌላኛው ደግሞ ንብረቴቹን የሚገዛ ደንበኛ አፈላላጊ ሆነው እየሰሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ፖሊስ የአዛውንቶቹን ሙሉ የስርቆት ሰንሰለት ካጠና በኋላ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሲሆን ወንጀሉን እንደፈጸሙ አምነዋል ተብሏል፡፡
አዛውንቶቹ ስርቆቱን ለምን እንደፈጸሙ ሲጠየቁም ኑሮ ከብዷቸው ህይወታቸውን ለማቆየት ብለው ወደ ስርቆት እንደገቡ ለፖሊስ ተናግረዋል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
የአዛውንት ህዝብ ብዛት በበዛባት ጃፓን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጡረታ በወጡ አባቶች የሚፈጸሙ ስርቆት ወንጀሎች እየጨመሩ መምጣታቸው ተገልጿል፡፡
በጃፓን በየዓመቱ ከሚወለዱ ህጻናት ይልቅ ጡረታ የሚወጡ አዛውንቶች ቁጥር ብልጫ አለው የተባለ ሲሆን ሀገሪቱ ዜጎቿ ጋብቻ እንዲመሰርቱ እና ልጆችን እንዲወልዱ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ዘርግታለች፡፡