”ምርጫ 2012” በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
ምርጫ 2012 በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንደማይካሄድ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
ምርጫው ነሀሴ 23፣2012ዓ.ም እንዲካሄድ እቅድ ተይዞለት ነበር፡፡
ቦርዱ ለምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ከስቀመጠ በኋላ ለምርጫ የሚሆኑ ግብአቶችን በማሟላት ሂደት ላይ እንደነበረ ሲገልጽ ነበር፡፡
ነገርግን ቦርዱ አለምአቀፋዊ በሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተያዘውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ፣ በሰሌዳው መሰረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ መወሰኑን አስታውቋል።
በዚህም ምክንያት በመጋቢት እና በሚያዚያ ወር 2012 ዓ.ም መጠናቀቅ ያለባቸው በርካታ ስራዎች መኖራቸውን የገለጸው ቦርዱ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ማካሄድ አይቻልም ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን 25 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
መንግስት የቫይረሱን መስፋፋት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፤ እየወሰደም ይገኛል፡፡
ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው እንዲቆዩ፣ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ እንዲሆኑና እንዲሁም ብዙ ህዝብ የሚሳተፍባቸው ስብሰባዎችም እንዲሰረዙ መንግስት ቀደም ብሎ ወስኖ ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መንግስት የዜጎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ በማሰብ የመንግስት መስሪያቤቶች እንዲዘጉና የኢትዮጵያ ድንበሮች ለሰዎች ዝውውር ዝግ እንዲሆኑ መወሰኑም የሚታወስ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የክልል መንግስታትም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡
የትግራይ ክልል “የአስቸኳይ ጊዜ” አዋጅ በማወጅ ሰዎች ከከተማ ወደ ገጠር እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ እንዳይንቀሳቀሱ እግድ የጣለ ሲሆን የአማራ ክልል ደግሞ ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ክልሉ የሚገቡ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንደማይኖሩ በትናንትናው እለት አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ የደቡብ ክልልም አዲስ አበባን ጨምሮ ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የሚደረጉ የህዝብ ትራንስፖርስት ስምሪት እንቋረጥ ወስኗል፡፡
በትናንትው እለት የኦሮሚያ ክልልም የህዝብ እንቅስቃሴን የሚገድብ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ መጋቢት 4፣ 2012 የተከሰተ ሲሆን አሁን ላይ በኦሮሚያና በአማራ ክልል መገኘቱ ተረጋግጧል፡፡