ኢሰመኮ ሴቶች በምርጫ ወቅት ለ“ወሲባዊ ጥቃቶች” እንደሚዳረጉ በጥናት ማወቁን ገለጸ
ኢሰመኮ በምርጫ 2013 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ከጥቃት እንዲከላከሉ ጠይቆ ነበር
ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርጫዎች የፍትሕ አካላት ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች መፍትሔ “የማይሰጡና በከፊልም እራሳቸው የችግሩ አካል እንደነበሩ” ገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሥርዓተ-ጾታ እኩልነት እና የሴቶች መብቃት ድርጅት ጋር በመተባበር አካሄድኩት ባለው ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች በምርጫ ወቅት ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ገልጿል፡፡
“መታገልን እንምረጥ” መሪ ቃል የሚከበረውን ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ፣ ኢሰመኮ
በምርጫ 2013 “በፖለቲካ ፓርቲ እጩነት፣ በመራጭነት፣ በምርጫ ፈጻሚነትና አስፈጻሚነት” የሚሳተፉ ሴቶች ለጥላቻ ንግግርና ለሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች እንዳይጋለጡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲከላከሉ ጠይቋል፡፡
ኢሰመኮ “በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በኦሮምያ እና በሶማሊ ክልሎች ላይ” አትኩሮ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በተለያየ መልኩ በምርጫ የሚሳተፉ ሴቶች የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም “ለዳሰሳው ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ሴቶች በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶቻቸውን መነጠቃቸውን፣ እስር፣ አካላዊና ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው፣ ከእምነት ቦታዎቻቸው መታገድ ጀምሮ እስከ በቤተሰብ መገለል ድረስ ለተለያዩ ችግሮች እንደተዳረጉ ያስረዳሉ” ብሏል ኢሰመኮ፡፡
ኢሰመኮ እንዳለው “በዳሰሳ ጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርጫዎች የፍትሕና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተገለጸው ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች መፍትሔ የማይሰጡና በከፊልም እራሳቸው የችግሩ አካል እንደነበሩ ታይቷል።”
ኢሰመኮ “በምርጫ 2013” ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሻሻል ስልት እንዲነድፍ መጠየቁ ይታወሳል፡፡