ምርጫ ቦርድ አብን “አግባብነት ያለው ምርጫ” እንዲያካሂድ ወሰነ
ፓርቲው ያሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ ረቂቅ ጉባኤው ከመካሄዱ ከ5 ቀናት በፊት ለምርጫ ቦርድ እንዲያቀርብ ተወስኗል
ምርጫ ቦርድ፣ አብን በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ ማለትም እስከ ሰኔ 18፣2014ዓ.ም ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ መወሰኑን አስታወቀ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ ወይም እስከ ሰኔ 18፣2014ዓ.ም ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ቦርዱ አብን ቀደም ሲል ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ መግባባት አልተደረሰበትም ያለውን “የአመራር ሪፎርም ወይም ለውጥ ማድረግ” በቀጣዩ ጉባኤ በአጀንዳነት እንዲያዝና እና ተገቢነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል፡፡
“ፓርቲው በደንቡ መሰረት የሚቀርጻቸውን ሌሎች አጀንዳዎች ጨምሮ በጉባኤ የመነጋገር መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ቀደም እልባት ያላገኘውን አጀንዳ ማለትም የአመራር ሪፎርም ወይም ለውጥ ማድረግ ለጉባኤው በአጀንዳነት ቀርቦ ተገቢ ውሳኔ እንዲሰጥበትና አግባብነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ“ ሲል ምርጫ ቦርድ ወስኗል፡፡
ምርጫ ቦርድ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፣ ቦርዱ የአብንን ጉባኤ እንዲሳተፉ የመደባቸው ባለሙያዎች ሪፖርት እና ቅሬታ አለን ያሉ የ308 ሰዎች ስምና ፊርማ ያለበት ቅሬታ መቅረቡን ተከትሎ ነው፡፡
በጉባኤው የተሳተፉ የቦርዱ ባለሙያዎች በምርጫ ቦርድ መመሪያ መሰረት፣ በፓርቲው የተደረጉ ማሻሻዎች እና የ2 አመት የፓርቲው የስራ እንቅስቃሴ ለጉባኤው ቀርቦ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን መታዘባቸውን ጠቅሷል ምርጫ ቦርድ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ምርጫ ቦርድ የአመራር ለውጥ እንዲደረግ በርካታ ጥያቄ የቀረበ ቢሆን በእለቱ ከመድረክ በኩል ጉባኤው የተጠራው ቦርዱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የመተዳደሪያ ደንብ ለማሻሻል እና ለማጽደቅ መሆኑን እና የአመራር ለውጥ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ እንዲካሄደ ማብራሪያ መሰጠቱን ታዝቢያለሁ ብሏል፡፡
ታዛቢዎቹ የፓርቲው አመራሮች የጉባኤውን መጠናቀቅ ተናግረው ከአዳራሽ መውጣታቸውን እና አብላጫ ቁጥር ያላቸው የጉባኤው አባላት የአመራሮቹን ከአዳራሽ መውጣት፣የአመራር ለውጥ አለመካሄዱን እና የመድረኩን መዘጋት መቃወመቸውን ቦርዱ መታዘቡን አስታውቋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ማሻሻያ የተደረገባቸው የመተዳደሪያ ደንብ አንቀጾች የተካተቱበት ረቂቅ ደንብ ጉባኤው ከመካሄዱ ከ5 ቀናት በፊት ለምርጫ ቦርድ እንዲያቀርብም ወስኗል፡፡