በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የሚመራው የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ኬንያ ገባ
ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እና ቡድናቸው ትናንት ማክሰኞ ናይሮቢ መግባታቸው ተሰምቷል
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በመጪው ማክሰኞ ይካሄዳል
በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የሚመራው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድን ኬንያ ገባ።
በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የሚመራው የምርጫ ታዛቢ ቡድን ትናንት ማክሰኞ ናይሮቢ መግባቱ ተሰምቷል።
በናይሮቢ በሚኖረው ቆይታ ከሃገሪቱ እና ከተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት ተወካዮች ጋር እንደሚወያይ ይጠበቃል።
ዶ/ር ሙላቱ በምርጫው የሚሳተፉትን ፖለቲከኞች ጨምሮ ሌሎችንም ከፍተኛ የኬንያ ባለስልጣናት አግኝተው ያነጋግራሉም ተብሏል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትናንት በኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪዎች ፎረም ለሰላም እና ለልማት (EFPD) የምስረታ ስነ ስርዓት ላይ ነበሩ።
በስነ ስርዓቱ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴም ተገኝተዋል።
ታዛቢ ቡድኑ ምርጫውን በገለልተኛነት ለመታዘብ በማሰብ ወደ ናይሮቢ ማቅናቱን ኢጋድ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ታዛቢ ቡድኑ ከቀጣናዊው ተቋም ስድስት አባል ሃገራት ማለትም ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ እና ከኡጋንዳ የተውጣጡ ሰባት ዋና እና 24 ጊዜያዊ አባላት የተዋቀረ ነው።
ከቋሚና ጊዜያዊ አባላቱ የተውጣጣና ቅድመ ምርጫ ግምገማን የሚያደርግ ቡድንም አለው።
ኢጋድ ከወር በፊት ከአፍሪካ ህብረት እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ባደረገው የቅድመ ምርጫ ግምገማ የኬንያን ዝግጁነት ማድነቁ ይታወሳል።
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በመጪው ማክሰኞ ይካሄዳል መባሉም የሚታወስ ነው።