ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከምክትላቸው ይልቅ ለተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ ድጋፍ መስጠታቸው ፉክክሩን አክሮታል ተብሏል
ተጠባቂው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሁለት ሳምንት ብቻ ቀርተውታል፡፡
ኬንያን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለመምራት እጩ ፕሬዝዳንቶች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን አገባደዋል፡፡
ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት አራት እጩዎች የቀረቡ ሲሆን ከእጩ ፕሬዝዳንቶች መካከል ባለፉት ምርጫዎች ላይ ለአራት ጊዜ ተወዳድረው ሽንፈትን ያስተናገዱት የኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ሙቭመንቱ ራይላ ኦዲንጋ ዋነኛው ተፎካካሪ ናቸው፡፡
ይህ ተጠባቂ ምርጫ የፊታችን ነሀሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም መካሄድ እንደሚጀምር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ራይላ ኦዲንጋ በፈረንጆቹ 1997 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራቸውን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት እጩ የነበሩ ሲሆን በምርጫው ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡
በነዳጅ እና ሀይል ልማት ዘርፍ ነጋዴ የሖኑት የ77 ዓመቱ ኦዲንጋ ላለፉት አራት ተከታታይ ፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ወቅቶች ላይ እጩ ቢሆኑም አብላጫ የህዝብ ድምጽ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡
ውጤታቸውን ተከትሎም ራይላ ኦዲንጋ ከፕሬዝዳናታዊ ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን ከአምስት ዓመት በፊት ቢናገሩም ዘግይተው በሰጡት መግለጫ ለአምስተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት መልሰው እንደሚወዳደሩ አሳውቀዋል፡፡
ኬንያን አሁን ላይ በምክትል ፕሬዝዳንትነት እያገለገሉ ያሉት የዲሞክራቲክ ዩኒየኑ ዊሊያም ሩቶ ሌላኛው ዋነኛ ተፎካካሪ ናቸው፡፡
የ55 ዓመቱ ሩቶ ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በግጭት ውስጥ ሲሆኑ የጸባቸው መንስኤ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ለራይላ ኦዲንጋ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ከዝቅተኛ ቤተሰብ እንደተገኙ እና በጥረታቸው ከድህነት እንደወጡ የሚናገሩት ሩቶ ኬንያ የሁለት ቤተሰቦች ሀገር አይደለችም ኬንያ የሑላችን ናት ሲሉ ለፕሬዝዳንት ኬንያን እና ራይላ ኦዲንጋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፤
ወጣቶች የተሻለ ሀብትና እና ለሀገራቸው አበርክቶ እንዲኖራቸው ልዩ ድጋፍ አደርጋለሁ የሚሉት ሩቶ ሙስና ዋነኛ የኬንያ ጠላት በመሆኑ በዚህ ዙሪያ በስፋት እሰራለሁ ሲሉ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ከራይላ ኦዲንጋ እና ዊሊያም ሩቶ በተጨማሪ ኬንያን በፕሬዝዳንትነት እየተፎካከሩት ያሉት ቀሪዎቹ እጩዎች ዳቪድ ዌሂጋ እና ጆርጅ ዋጃኮያህ ናቸው፡፡
በዚህ ምርጫ ላይ አዲስ ነገር ይዘው ብቅ ያሉት እጩ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋጃኮያህ ማሪዋና ዕጽ በይፋ እንዲመረት ህጋዊ ፈቃድ እንደሚሰጡ እንዲሁም የእባብ መርዝን በማምረት ውደ ውጪ ሀገር የሚላክበትን ስርዓት በመዘርጋት ለወጣቶች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ኬንያን ላለፉት 10 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት ኡሁሮ ኬንያታ የስልጣን ጊዜያቸውን ከሁለት ጊዜ በላይ ማራዘም ስለማይችሉ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት እንዲያስረክቡ የሀገሪቱ ህገ መንግስት ያስገድዳቸዋል፡፡