“ከምርጫ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ የማድረጉ ጉዳይ በቂ ትኩረት አላገኘም”- እንባ ጠባቂ
በመረጃ እጦት ምክንያት ህዝቡ “ለአሉባልታ ወሬና ለሀሰተኛ መረጃ መጋለጡን”ም ነው ዕንባ ጠባቂ ያስታወቀው
ምርጫ ቦርድ መሠረታዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ እያደረገ ቢሆንም ጥረቱ በቂ እንዳይደለም ተቋሙ አስታውቋል
ከመጪው ሃገራዊ ምርጫ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ረገድ ውስንነቶች እንዳሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡
“ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱ ከተጀመረበት እለት ጀምሮ መሠረታዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ እያደረገ ቢሆንም በቂ አይደለም” ያለው ተቋሙ “መረጃን አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ የማድረጉ ጉዳይ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ዘንድ በቂ ግንዛቤና ትኩረት አግኝቷል ማለት” እንደማይቻል ገልጿል፡፡
“ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ዘንድ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት” አለመቻሉንም ነው ዕንባ ጠባቂ ያስታወቀው፡፡
በዚህም “ለአሉባልታ ወሬና ለሀሰተኛ መረጃ መጋለጡን ልብ ይሏል”ም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 13 በመንግስታዊ አካላት ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ ስለታዘዙ መረጃዎች ዝርዝር ማብራሪያ የማዘጋጀት ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡
የመረጃ ነጻነት አፈጻጸምን አስመልክቶ አሰራሮችን ለማዳበር እና ለማሻሻል የሚረዱ አጠቃላይና ወይም ዝርዝር የውሳኔ ሀሳቦችን ለመንግስታዊ አካላት የማቅረብ ሃላፊነትም አለው፡፡
በዚህም መሠረት የሚታዩትን ዋና ዋና ክፍተቶች እንዲሻሻሉ የውሳኔ ሀሳብ ለማቅረብ ይረዳው ዘንድ የክትትልና ድጋፍ መመሪያ (ጋይድ ላይን) አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን ነው ያስታወቀው፡፡
ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች የምርጫው ተዋናይ የሆኑ አካላት ከምርጫው ጋር የተያያዙ የቅድመ- ምርጫ፣የምርጫ ዕለትና የድህረ- ምርጫ መረጃዎችን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ እንዲያደርጉም አሳስቧል፡፡