የሐረሪ ክልል የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ተቃወመ
ቦርዱ ከክልሉ ውጭ ያሉ ሐረሪዎች በክልሉ ብሔራዊ ጉባኤ ምርጫ እንዲሳተፉ የቀረበለትን ጥያቄ አለመቀበሉ የሚታወስ ነው
በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባን ያደረገው የክልሉ ምክር ቤት የቦርዱን ውሳኔ “ሕገ መንግስታዊ ይዘትም ሆነ ሕጋዊ ተቀባይነት የለውም” ሲል ገልጿል
የሐረሪ ክልል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሰሞኑ ያሳለፈውን ውሳኔ ተቃወመ፡፡
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ቦርዱ ከክልሉ ውጭ ያሉ ሐረሪዎች በክልሉ ብሔራዊ ጉባኤ ምርጫ እንዲሳተፉ የቀረበለትን ጥያቄ አለመቀበሉን ተከትሎ ትናንት ሚያዚያ 3/2013 ዓ.ም አስቸካይ ስብሰባን አካሄዷል፡፡
በስብሰባው የቦርዱን ውሳኔ አስመልክቶ ውሳኔዎችን ማስተላለፉንም ነው በክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ በኩል ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው፡፡
በውሳኔው “ቦርዱ ሚያዚያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ያስተላለፈው ውሳኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 6 ቀን 1987 ዓ.ም ባካሄደው 102ኛ መደበኛ ስብሰባ ያሳለፈውን ውሳኔ፣ የክልሉን ሕገ መንግስት እና የምርጫ ሕጉን በሚጻረር መልኩ የተሰጠ ነው” ብሏል፡፡
ውሳኔው “ሕገ መንግስታዊ ይዘትም ሆነ ከሕግ አንጻር ተቀባይነት” እንደሌለውም ነው የገለጸው።
“የሀረሪ ጉባኤ እና የፌደራል ህዝብ ተወካይ ልዩ ውክልና ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ አይደለም” ያለው ምክር ቤቱ “የቦርዱ ውሳኔ ህገመንግስትዊ፣ ህጋዊ፣ ፍትሃዊ እና አመክንዮአዊ ያልሆነ እና የክልሉን ሕገ መንግስት ያላማከለ መሆኑን በመጠቆም ከሕግ አንጻር ተቀባይነት እንደሌለው” አስታውቋል።
የክልሉ ሕገ መንግስትና የሕግ የበላይነት እንዲሁም በፌደራል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የተላለፈ ውሳኔ ሊከበር” እንደሚገባ በማሳሰብም “ችግሮቹን ለማረም የሚችል አግባብነት ያለው አካል ተቋቁሞ ተገቢው የእርምት እርምጃ እንዲደረግ” የክልሉ ካቢኔ ስለመወሰኑም ገልጿል።
ከአሁን ቀደም በተካሄዱት 5 ሃገራዊ ምርጫዎች ከክልሉ ውጭ ያሉ ሐረሪዎች በክልሉ ብሔራዊ ጉባኤ ምርጫ ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
ይህን በማስታወስም ክልሉ ዘንድሮም ከክልሉ ውጭ ያሉ ሐረሪዎች ድምጽ እንዲሰጡ እና በምርጫው እንዲሳተፉ ቦርዱን በደብዳቤ ጠይቆ ነበር፡፡
ሆኖም ቦርዱ “በሕገ መንግስቱ መሠረት በአንድ ክልል የመንግስት አወቃቀር ውስጥ የሚገኙ የምክር ቤት አባላት መመረጥ የሚኖርባቸው በክልሉ ድምፅ መስጠት በሚችሉ ነዋሪዎች ነው” በሚል ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
ተቋማዊ ለውጥ ማድረግ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት “እንዲህ ዓይነት የሕገ መንግስትና የምርጫ ሕጉ መሠረት የሌላቸውን ልምዶችና አሰራሮች እንዳይቀጥሉ” ለማድረግ በማሰብ ጭምር መሆኑንም ነው ቦርዱ በወቅቱ ያስታወቀው፡፡
ቦርዱ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔን የምርጫ ምልክት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡