“የአማራ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደምርጫ ሂደት እየገባ እንደሆነ እናምናለን”- በለጠ ሞላ፣ የአብን ሊቀመንበር
በዴሞክራሲ የሚያምኑ ኃይሎች “በመልዕክቱ አይረበሹም” ሲሉም ገልጸዋል
ሊቀመንበሩ “‘ጊዜው አሁን ነው’ያልነውም ለዚህ ነው” ብለዋል
አል ዐይን አማርኛ ሀገራዊ የምርጫ ዝግጅትና የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋትን በተመለከተ ከሰሞኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር ቆይታ እያደረገ ነው፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ ከአል ዐይን ጋር ቆይታ ካደረጉ የፖለቲካ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ሊቀመንበሩ የንቅናቄውን የምርጫ ዝግጅትና መሰል ጉዳዮች በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አብን ከሰሞኑ “ጊዜው አሁን ነው” የሚል መልዕክትን በአመራሮቹ እና በአባላቱ በኩል በየማህበራዊ ገጹ አሰራጭቷል፡፡
መልዕክቱን የማህበረሰብ አንቂዎች (አክቲቪስቶች) ፣የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ሌሎችም ፖለቲካ ይመለከተናል ያሉ አባላት ተቀባብለውታል፣ ተነጋግረውበታል፣ ተከራክረውበታልም፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች በመልዕክቱ ዙሪያ አጸፋዊ ምላሽን ሲሰጡም ተስተውሏል፡፡
“ጊዜው አሁን ነው” አጠቃላይ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት መሆኑን የገለጹት አቶ በለጠ የአማራ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደምርጫ ሂደት እየገባ እንደሆነ በማመን መልዕክቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
“የአማራ ሕዝብ እስካሁን፤ በተለይ ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት፤ የመጣበትን ታሪካዊ ሂደት አስመልክቶ ሲገመገም ዘንድሮ የሚደረገው ምርጫ እንደ ሕዝብ የተሻለ ነገር መስራት ይቻል ዘንድ ይህንን ጊዜ መጠቀም እንዳለበት የሚገልጽ መልዕክት ነው”ም ነው ሊቀመንበሩ ያሉት፡፡
ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ አምስት ምርጫዎች ተደርገዋል፡፡ ሆኖም እነሱን ምርጫ ብሎ መጥራት ይቸግራል እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፡፡
“በእርግጠኝነት መናገር የምንፈልገው የአማራ ሕዝብ ነቅቶ፣ ተደራጅቶ ለሚፈልገው፣ ለሚያምንበት የፖለቲካ ድርጅት ድምጹን መስጠት የሚችልበትና ነገውን በተሻለ መወሰን የሚችልበት ምርጫ ለማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ምርጫ ሂደት እየገባ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ስለዚህ ጊዜያችን አሁን ነው የሚል መልዕክት መርጠናል” ብለዋል፡፡
የምርጫውን ወሳኝነት በመጠቆም ሕዝቡ ይህንን ጊዜ መጠቀም እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡
የመልዕክቱን አነጋጋሪነት በተመለከተ ሊቀመንበሩ “አንዳንድ ኃይሎች ብዙም ሊገባን ባልቻለ መልኩ የመደናገጥ አይነት ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል” ሲሉ መልሰዋል መልዕክቱ እዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚከት እንዳልነበር በማከል፡፡
“በመልዕክቱ የተደናገጡ ኃይሎች ድምጽን በማፈን፣ በተቋማት ውስጥ የአንድ ወገን የበላይነት በማስፈን፣ ሕጎች ለአንድ ወገን ያዘመሙ እንዲሆኑ እና ይህን ለማስተግበር የሚሰሩ ናቸው፡፡ ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰፍን የማይፈልጉ በመሆናቸው እንዲህ አይነት ሕዝብን ማነቃነቅ የሚችል ጠንካራ መልዕክት ሲመጣ መደናገጣቸው የሚቀር አይደለም” ብለዋል አቶ በለጠ ፡፡
ይሁንና “የመደናገጥ አይነት ባህሪ የሌላቸው፤ በዴሞክራሲ የሚያምኑ ኃይሎች በመሰል መልዕክቶች ፈጽሞ ሊሸበሩ” እንደማይችሉ ነው ሊቀመንበሩ የተናገሩት፡፡
አንዳንድ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች መልዕክቱን “ከአውዱ ውጭ” ተረድተዋልም ብለዋል፡፡
“በተለይ የኦሮሞ ብልጽግና የሚባለው ኃይል፤ በአንዳንድ ጽንፈኛ ሰዎች እየተመራ፤ ይህንን መልዕክት ከአውዱ ውጭ በመተርጎም ለራሳቸው በመሰላቸው ትርጉም ለመስጠት ” መሞከራቸውንም ነው ያስቀመጡት፡፡
መልዕክትን እንዲህ ባለ መንገድ “የሚተረጉሙና የሚደናገጡ ኃይሎች፤ ከዴሞክራሲ ባህል ያፈነገጡ መሆናቸውን ከማጋለጥ ውጭ” ሌላ ጉዳይ እንደሌለውም ገልጸዋል፡፡
አብን ሃገራዊ ፓርቲ ሆኖ ነው በምርጫ ቦርድ የተመዘገበው፡፡ ሆኖም አንዳንዶች ከአካሄዱ ጋር በተያያዘ በጽንፈኝነት ይወቅሱታል፡፡ ይህን በተመለከተ አል ዐይን የጠየቃቸው ሊቀመንበሩ
“አንዳንዶች ጉዳዮችን በጥልቀትና በስፋት የማየት ተፈጥሯዊ ውስንነት አለባቸው፡፡ አብንን ጽንፈኛ ብሎ ሊከስ የሚችል ኃይል ምናልባት ወይ አልገባውም፤ ወይ እኛን በተሻለ ለመረዳት አልቻለም ወይንም ደግሞ ራሱ ጽንፈኛ ሆኖ በራሱ ሚዛን ሌሎችን እያየ የሌሎችን ሀቀኛ እንቅስቃሴ ለማየት፣ለመረዳት አቅም ያነሰው ካልሆነ በስተቀር አብን ጽንፈኛ ሊባል የሚችልበት አንዳችም ምክንያት የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አብን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ አትዮጵያ በጣም አስቸጋሪ ምዕራፍ ውስጥ ስትገባ ግንባር ቀደም ሆኖ ሀገርን ያዳኑ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የገለጹት አቶ በለጠ ይህም ለብዙዎች እፎይታን የፈጠረ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ንቅናቄው በማንነታቸው ምክንያት መገፋትና በደል የደረሰባቸው ሕዝቦች አጋር ሆኖ መቆሙን ያነሱም ሲሆን በኢትዮጵያ የሁሉም ሕዝቦች ነጻነት፣ እኩልነትና ፍትህ ተረጋግጦ ማየት እውነተኛ ማንነቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
“አንዳንዶች የአማራ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጠንካራ ሆኖ ወደፊት እንዲመጣ አይፈልጉም፤ ጠንካራ ሆኖ በመጣ ጊዜ ወይም እንደዛ ሆኖ መጥቷል ብለው ባሰቡ ጊዜ ሽብር ውስጥ የሚገቡ ኃይሎች እንዳሉ እናውቃለን” ሲሉም ነው ሊቀመንበሩ የሚናገሩት፡፡
ይህ እንዳይሆን የሚፈልጉ አካላት “በዋናነት በመንግስት መዋቅር ውስጥ” እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
ከዚያ ውጭ ያሉ ኃይሎች በመንግስት ስር ካሉት ጋር ትስስር በመፍጠር “እንደዚህ አይነት ወጥነት ያለው እንቅስቃሴ፤ ጩኸት ሲያደርጉ እንሰማለን” ያሉም ሲሆን ነገሮችን የሚያዩበት ስፋትና ጥልቀት እጥረት ስላለበት ነው በሚልም ምክንያቱን ያስቀምጣሉ፡፡
አቶ በለጠ “የአብን መነሻም፤ መድረሻም ኢትጵያዊነት” መሆኑን አንስተው ይህንን ግን መናገር እንደማይጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡