አቶ ዛዲግ በትግራይ ክልል ምርጫው የመካሄድ “እድል አለው” አሉ
በክልሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው የሰብአዊ እርዳታ እንደሚፈልግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል
ለምርጫ ሲባል “ህትመቱ ትግራይም ታትሟል፤ ስልጠናም እየተሰጠ ነው” ብለዋል አቶ ዛዲግ
የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ በመጭው ግንቦት ወር እንዲካሄድ የተወሰነው ጠቅላላ ምርጫ በትግራይ ክልልም የመካሄድ እድል እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በምርጫ ቦርድ ስብሰባ መካፈላቸውን የገለጹት አቶ ዛዲግ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል ምርጫ አይካሄድም አለማለቱን፤ ነገርግን በጊዜያዊነት ከምርጫ ሰሌዳ ማውጣቱንና ሁኔታውን አይቶ እንደሚወስን ነው ያስታወቀው ብለዋል፡፡
“ህትመቱ ትግራይም ታትሟል፤ ስልጠናም እየተሰጠ ነው” ያሉት አቶ ዛዲግ “እንደምናየው እድል አለው አብረን ብናየው ጥሩ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ብልጽግና በትግራይ አባላት እንዳሉትና የምልመላ ስራ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በባለፈው ጥቅምት ወር ወደ ጦርነት ካመራ በኋላ በትግራይ ክልል የጸጥታ መደፍረስ አጋጥሞ ቆይቷል፡፡
በሁለቱ መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ግጭት ያመራው የትግራይ ክልልን ይመራ የነበረው ህወሓት ከምርጫ ቦርድ ተቃራኒ በመቆም የራሱን ክልላዊ ምርጫ ቦርድ በማቋቋሙና ምርጫ በማካሄዱ ነበር፡፡
የፌደራል መንግስት “የህግ ማስከበር” ባለው ዘመቻ የህወሓት አባላትንና ተባባሪ ነበሩ ያላቸውን ወታደራዊ ቡድኖች በማደን ላይ ሲሆን እስካሁን ከቀድሞ የህወሃት አመራሮች መካከል የተያዙ፤የተገደሉና፤እየተፈለጉ ያሉም አሉ፡፡
በትግራይ ክልል በግጭቱ ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆሩ ሰዎች ለረብ መዳረጋቸውን በእነ ዶ/ር ሙሉ ነጋ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ በክልሉ ሰብአዊ ቀውስ መከሰቱን የተለያዩ የመብት ድርጅቶችም እየገልጹ ነው፡፡
የፌደራል መንግስት ግጭት ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሰብአዊ እርዳታ የሚውል ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን እየላከ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡