“አቶ ዳውድ ኢብሳ ያስገቡትን የምርጫ ምልክት አንቀበልም” አቶ ቀጄላ መርዳሳ
ምልክቱ የገባው በኦነግ መዋቅር እንዳልሆነ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገልጸዋል
ኦነግ የምርጫ ምልክት ካስገቡ ፓርቲዎች መካከል መሆኑን የምርጫ ቦርድ ገልጿል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የፓርቲዎች የምርጫ ምልክት መረጣ እየተከናወነ መሆኑን ቦርዱ ገልጿል፡፡ በዚህም መሰረት እስከ አሁን ድረስ 45 ፓርቲዎች ምልክቶቻቸውን ማስገባታቸው የተገለጸ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አንዱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ነው፡፡
ኦነግ በሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ በኩል የምርጫ ምልክት ማስገባቱን ቦርዱ የገለጸ ቢሆንም ፣ ከድርጅቱ አንዳንድ አመራሮች ግን ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ቀደም ሲል በኦነግ አመራር አባላት መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ጉዳዩ በምርጫ ቦርድ መያዙ ይታወሳል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበርም ሆነ በሊቀመንበሩ ታግደዋል የተባሉት ስራ አስፈጻሚዎች ህጋዊ የድርጅቱ አካላት ሆነው እንደሚቀጥሉ ቦርዱ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ይሁንና የአመራር አባላቱ በምርጫ ምልክት ምክንያት መግባባት ላይ አለመድረሳቸው እየተገለጸ ነው፡፡
አቶ ዳውድ ኢብሳ የምርጫ ምልክት ማስገባታቸውን በተመለከተ በቦርዱ የተሰጠውን ገለጻ የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ተቃውመዋል፡፡
አቶ ቀጄላ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ ፣ አቶ ዳውድ ያስገቡት የምርጫ ምልክት “በአመራር ደረጃ ውይይት ያልተደረገበትና ለድርጅቱ የማይመጥን” መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ምልክቱ ላይ አልተወያየንበትም ፤ አንቀበለውም” ያሉት አቶ ቀጄላ ፣ ይህንን በተመለከተ ትናንት ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ ማስገባታቸውን ለአል ዐይን ኒውስ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳውድ የምርጫ ምልክቱን ያስገቡት የድርጅቱን መዋቅር ተጠቅመው ሳይሆን የማይመለከተውን ሰው በመላክ እንደሆነ ነው አቶ ቀጄላ ያስታወቁት፡፡ ምልክቱ መግባት ያለበት “ቀጥታ በራሳቸው አሊያም በሕግ ግንባሩን በሚወክል ሰው መሆን ይገባው እንደነበር“ ገልጸው “ምርጫ ቦርድ እየቀለደ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ በሰጠው መግለጫ ህጋዊ ኃላፊነት በተሰጠው አካል ምልክታቸውን እንዲመርጡ በተጠየቀው መሰረት “የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የምርጫ ምልክት አስገብተዋል” ነው ያለው።
“ምልክቱ በሹፌራቸው አማካኝነት ነው የገባው” የሚሉት አቶ ቀጄላ ግን የገባውን ምልክትና አጠቃላይ ሂደቱን እንደማይቀበሉት በመግለጽ ቅሬታ ማስገባታቸውን አስታውቀዋል፡፡ አቶ ዳውድ ለቦርዱ ያስገቡት ምልክት ‘የቡና ፍሬ’ እንደሆነ የገለጹት አቶ ቀጄላ ‘ቡና ብዙ ቦታ ስላለ’ ሌሎች አማራጭ ምልክቶችን መጠቀም ይቻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ቦርዱ ሁለቱ ወገኖች በጋራ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያከናውኑ ታህሳስ ላይ ውሳኔ ማስተላለፉ የሚታወስ ሲሆን ለዚህ ዝግጅትም ሁለቱም ወገኖች የሚገኙበት የመጀመሪያ ስብሰባ በቦርዱ የስበሰባ አዳራሽ እንዲከናወን ወስኖ ነበር፡፡ ይሁንና ይህንን የቦርዱን ውሳኔ አቶ ዳውድ ኢብሳ እንዳልተቀበሉት ነው አቶ ቀጀላ የገለጹት፡፡
በዚሁ ጉዳይ አቶ ዳውድ ኢብሳን በስልክ ለማናገር ሙከራ ብናደርግም የእጅ ስልካቸው ሊሰራ ባለመቻሉ አልተሳካልንም፡፡