የጦር አዛዡ ባሻር ኑርዛይን ታሊባን ወደ ትጥቅ ትግል ሲገባ ለቡድኑ “የጦር መሳሪያ ድጋፍ” ሲያደረግ የነበረ ነው ተብሏል
ታሊባን በአሜሪካ እጅ የነበረውን የጦር አዛዥ ለማስፈታት ከሁለት አመት በላይ ታስሮ የነበረውን አሜሪካዊ የባህር ኃይል አርበኛ ለዋሽንግተን አሳልፎ መስጠቱን አስታወቀ፡፡
የአፍጋኒስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካን ሙታቂ በካቡል ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ዛሬ ማርክ ፍሬሪችስ ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጥቷል ፤ እኛም የጦር መሪው ሃጂ ባሻር ኑርዛይ በካቡል አየር ማረፊያ ተሰጥቶናል" ብለዋል።
ልውውጡ የተከናወነው “ከረጅም ድርድር በኋላ” መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በካቡል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አንድ የሀገራችን ልጅ ወደ ሀገሩ ሲመለስ የነበረውን አስደናቂ ስነ ስርዓት በማየታችን ደስተኛ ነን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኑርዛይ በአውሮፕላን ማረፊያው ሲደርስ በአዲሱ የአፍጋኒስታን እስላማዊ ኢሚሬትስ (አይኢኤኤ) መንግስት የጀግና አቀባበል እንደተደረገለትም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
በማህበራዊ የትስስር ገጾች በመዘዋወር ላይ ያሉ ፎቶዎች የሚያሳትም፤ኑርዛይን የአበባ ጉንጉን በያዙና ጭንብል በለበሱ የታሊባን ባለስልጣናት አቀባበል ሲደረግለት ነው፡፡
ለበርካታ አመታት በአሜሪካ እጅ የቆየው የጦር አዛዡ ባሻር ኑርዛይ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ በሰጠው መግለጫ የታሊባን አመራሮች እሱን ለመስፈታት የተጓዙት የድርድር ርቀት አድንቋል፡፡
“ታሊባን ጠንካራ ቁርጠኝነቱን ባያሳይ ኖሮ ዛሬ እዚህ ባልነበርኩ ነበር” ብሏል ኑርዛይ።
ባሻር ኑርዛይ - ከሄሮይን ኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ ለ17 ዓመታት በአሜሪካ ታስሮ የቆየ የጦር አዛዥ ሲሆን ማርክ ፍሬሪችስ ደግሞ እንደፈረንጆቹ በ2020 ታፍኖ ተወስዶ በታሊባን ቁጥጥር ስር የቆየ የአሜሪካ የባህር ኃይል አርበኛ ነው፡፡
የአሜሪካ የባህር ኃይል አርበኛው ማርክ ፍሬሪችስ በአፍጋኒስታን ውስጥ በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በሲቪል መሃንዲስነት ሲሰራ የነበረ እንደሆነም ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የገለጸው፡፡
ኑርዛይ በታሊባን ውስጥ ምንም አይነት ኦፊሴላዊ ቦታ አልነበረውም ነገር ግን በ 1990 ዎቹ ውስጥ ጠንካራው እንቅስቃሴ ብቅ ባለበት ወቅት “ጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ ለታሊባን ጠንካራ ድጋፍ ያደረግ ነበር” ያሉት ደግሞ የአፍጋኒስታን መንግስት ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ናቸው፡፡
ከአንድ አመት በፊት የአሜሪካና አጋሮቿ ጦር ከ20 ዓመታት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በኋላ አፍጋኒስታንን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ፤ ታሊባን አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው፡፡