ናይጄሪያዊው ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ በ19 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር 105ኛው የዓለማችን ቱጃር ሆኗል
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አምራቹ ቴስላ ሞተርስ ባለቤት የሆነው ኤለን መስክ ቁጥር አንዱ የዓለማችን ቱጃር ሆነ፡፡
ኤለን መስክ የግዙፉን የዓለማችን የበይነ መረብ መገበያያ ባለቤት ጄፍ ቤዞስን በመብለጥ ነው ቁንጮ የዓለማችን ቱጃር የሆነው፡፡
የኒውዮርክ ዕለታዊ የአክስዮን የግብይት ዋጋ ተከታትሎ የቱጃሮቹን ሃብት የሚያሰላው ብሉምበርግ በቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ዘርፍ ላይ የተሰማራው መስክ የተጣራ 236 ቢሊዮን ዶላር አለው ብሏል፡፡
መስክ ስፔስ ኤክስ የተባለ ሮኬት አምራች ኩባንያ እንዳለውም ይታወቃል፡፡
በቅርቡ ወደ ጠፈር ተጉዞ የነበረውና የዓለማችንን የቱጃሮች ዝርዝር በቀዳሚነት ይመራ የነበረው ሌላኛው አሜሪካ ጄፍ ቤዞስ በ197 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛው ቱጃር ነው፡፡
ቤዞስ ብሉ ኦርጅን የተሰኘ የመንኮራኮሮች አምራች ኩባንያ ባለቤት ነው፡፡ ብሉ ኦርጅን የጠፈር ቱሪዝምን ለማስፋፋት እና ጉዞዎችን ለማድረግ በማሰብ የተቋቋመ ነው፡፡
ፈረንሳዊው ቢሊዮኔር በርናርድ አርኖልት ደግሞ በ164 ቢሊዮን 3ኛው የዓለማችን ቱጃር ነው፡፡
በርናርድ በሃብት ደረጃው ከአውሮፓ ቀዳሚው ነው፡፡ በስራ በርካታ የንግድ ተቋማትን የሚያስተዳድረው ኤል ቪ ኤም ኤች የተሰኘው የበርናርድ ኩባንያ ውድ መጠጦችንና ሽቶዎችን ጨምሮ የተለያዩ የቅንጦች እቃዎችን ያመርታል፡፡
የማክሮሶፍት ኩባንያ መስራቹ ቢል ጌትስ፣ የጎግል መስራቾቹ ላሪ ፔጅ እና ሰርጊ ብሪን ተከታዮቹን የቱጃርነት ደረጃዎች ይይዛሉ፡፡
ህንዳዊው ቱጃር ሙከሽ አምባኒ 11ኛ በመሆን የዓለማችንን ቀዳሚ ቱጃሮች ጎራ ለመቀላቀል ችሏል፡፡ የሪሊያንስ ኩባንያ ባለቤቱ አምባኒ የ102 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት ነው፡፡
በነዳጅ ማጣራትና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ የተሰማሩ ሌሎችንም ድርጅቶች ያቀፈው ሪሊያንስ የክሪኬት ቡድንን ጨምሮ ግዙፍ የበይነ መረብ የግብይት ተቋማትንም ያስተዳድራል፡፡
ናይጄሪያዊው ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ በ19 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር 105ኛው የዓለማችን ቱጃር ሆኗል፡፡ የተለያዩ የነዳጅ እና ሲሚንቶ አምራች ኩባንያዎችን የሚያስተዳድረው ዳንጎቴ ከአፍሪካ ቀዳሚው ቱጃር ነው፡፡
ሩሲያዊውን ቱጃር ሮማን አብራሞቪችን በመብለጥ ነው 105ኛ የሆነው፡፡ የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ቼልሲ ባለቤት የሆነው አብራሞቪች በ19 ቢሊዮን ዶላር 106ኛ ነው፡፡