ቢሊየነሩ መስክ ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ እንደሚዘዋወሩ ገልጸዋል
ትዊተር አዲስ ዋና ስራ አስፈጻሚ መቅጠሩን አስታውቋል።
ኢለን መስክ እስካሁን ስማቸው ያልተጠቀሱ ሴት ስራ አስፈጻሚ በስድስት ሳምንታት ውስጥ ማህበራዊ የትስስር ገጹን እንደሚረከቡ ተናግረዋል ።
ቢሊየነሩ በትዊተር ገጻቸው ውሳኔውን ያበሰሩ ሲሆን፤ "የእኔ ሚና ወደ ኤክሴክ ሊቀመንበር እና የቴክኖሎጂ ዋና ኃላፊ በመሆን ምርትንና ሶፍትዌሮችን ወደ መቆጣጠር ይሸጋገራል" ብለዋል።
አዲሷ ስራ አስፈጻሚ "ኤክስ" የተባለውን የትዊተር ክንፍ እንደሚመሩ ተነግሯል።
ይህ ክንፍ መስክ የተለያዩ ስራዎች በወላጅ ኩባንያው የሚሰሩበትና ቢሊየነሩ ትዊተርን ከማህበራዊ አውታር መረብ ባለፈ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሰጪ አድርገው ለመቀየር እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።
ኢንዲፔንደንት ዌል ስትሪት ጆርናልን ጠቅሶ እንደዘገበው የኤንቢሲ ዩንቨርሳል የማስታወቂያ ኃላፊ የሆኑት ሊንዳ ያካሪኖ በቲዊተር የዋና ስራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ለመረከብ እየተነጋገሩ ነው ብሏል።
ከኩባንያው ጋር ከአስር ዓመታት በላይ የቆዩት ያካሪኖ ለድርጅቱ አዲስ እሳቤ አበርክቷቸው የጎላ ነው ተብሏል።