“በትዊተር ቢሮ እያደርኩ የምሰራበት ጊዜ አለ” - ኤለን መስክ
ትዊተርን መምራት “ህመም” አለው ያለው የአለማችን ሁለተኛው ባለጸጋ፥ እውነተኛ ገዥ ከመጣ ትዊተርን መሸጥ እንደሚፈልግ ገልጿል
መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊየን ዶላር መግዛቱ ይታወሳል
የአለማችን ሁለተኛው ባለጠጋ ኤለን መስክ ትዊተርን ከገዛ በኋላ እጅግ አድካሚ ጊዜ እያሳለፈ መሆኑን ተናገረ።
ቢሊየነሩ በሳንፍራንሲስኮ ከቢቢሲ ጋር ቃለምልልስ አድርጓል።
ትዊተርን መምራት “ህመም አለው” የሚለው ኤለን መስክ፥ በዳኛ ውሳኔ እንደሚገደድ ሲያውቅ ኩባንያውን መግዛቱን ገልጿል።
መስክ በ44 ቢሊየን ዶላር ትዊተርን ከመግዛቱ በፊት የግዥ ውሳኔውን ለመሰረዝ አስቦ እንደነበር ይታወሳል።
ትዊተርን በስራ አስፈጻሚነት እየመራ የሚገኘው መስክ፥ የሚተካኝ ሰው ከተገኘ ሃላፊነት እለቃለሁ ቢልም እስካሁን ግዙፉን ኩባንያ መምራቱን ቀጥሏል።
ኩባንያውን መምራት ፈታኝ መሆኑን በቃለምልልሱ ያነሳው ቢሊየነሩ፥ አንዳንዴ ቢሮ ውስጥ እንደሚያድር ገልጿል።
ባለፉት ወራት “የሚደብር” ጊዜ ማሳለፉን ነገር ግን ኩባንያው በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም ነው ያነሳው።
ትዊተርን መግዛቱ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ይጠቅስና ሀቀኛ ገዥ ከመጣ ግን ለመሸጥ አላቅማማም የሚል ሃሳቡንም ያስከትላል መስክ።
ቢሊየነሩ ትዊተርን ከመግዛታቸው በፊት ኩባንያው 8 ሺህ ሰራተኞች ነበሩት። አሁን ላይ ግን ወደ 1 ሺህ 500 ዝቅ ብሏል።
“በግል ማንንም ከስራ አላባረርኩም” የሚል ምላሽ የሰጠው መስክ፥ የሰራተኞቹ ቅነሳ መጠነኛ መንገራገጭ መፍጠሩን አልሸሸገም።
አሁን ግን በአነስተኛ የሰው ሃይል ትዊተር በሚገባ ስራውን መቀጠሉንና ከኪሳራ እንደሚወጣም ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቃለምልልስ ገልጿል።