የትዊተር ተጠቃሚዎችን እያስኮበለለ ያለው “ማስቶዶን” መተግበሪያ
የጀርመኑ የማህበራዊ ትስስር ገጽ “ማስቶዶን”፥ ኤለን መስክ ትዊተርን ገዝቶ አወዛጋቢ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ ብዙዎች አማራጭ አድርገውታል
ከስድስት አመት በፊት ይፋ የተደረገው የማህበራዊ ትስስር ገጽ በህዳር ወር 2022 ብቻ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ከአራት እጥፍ በላይ ጨምሯል
አሜሪካዊው ቢሊየነር ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊየን ዶላር መግዛታቸው ከተሰማ በኋላ የትዊተር ተጠቃሚዎች ማስቶዶን ወደተሰኘው አምሳያው እየኮበለሉ ነው ተብሏል።
ማስቶዶን ከስድስት አመት በፊት የተቋቋመ ቢሆንም፥ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በእጥፍ የተመነደገው በ2022 ነው።
ኤለን መስክ ትዊተርን ከመግዛቱ በፊት 500 ሺህ ተጠቃሚ የነበረው ማስቶዶን፥ በህዳር ወር አጋማሽ 2022 ከ2 ሚሊየን በላይ ቋሚ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል።
የማህበራዊ ትስስር ገጹን በየቀኑ የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥርም እስከ 650 ሺህ ደርሶ እንደነበር ነው ዘጋርዲያን ያስነበበው።
- “አርቲፋክት” የኢንስታግራም መስራቾቹ የፈጠሩት አዲሱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ
- ኢትዮጵያ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በራሷ ለማልማት የያዘቸው እቅድ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
የጀርመኑ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ማስቶዶን ጂ ኤም ቢ ኤች ኩባንያ ያስተዋወቀው የማህበራዊ ትስስር ገጽ አንድ ባለቤት የለውም።
እንደ ትዊተር እያንዳንዱ ትዊቶች እና አስተያየቶች ከአንድ ማዕከል በብቸኝነት ቁጥጥር አይደረግባቸውም።
ማስቶዶን ለተለያዩ ጉዳዮች ራሳቸውን የቻሉ ሰርቨሮች እንዲኖሩ በማድረግ የይዘቶችን በአንድ ማዕከል ብቻ በቁጥጥር ስር መውደቅ ይታደጋል።
የቴክኖሎጂ፣ የጤና፣ የፖለቲካ፣ የቢዝነስ እና ሌሎች የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው ተቋማት የራሳቸው ሰርቨር እንዲኖራቸው በማድረግ ከሌሎች መሰል ኩባንያዎች ጋር የማስተሳሰር ስራንም ለመከወን ያስችላል።
የማስቶዶን ተጠቃሚ ሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጹን ተጠቃሚዎች ሲከተል (ፎሎው ሲያደርግ) እና መልዕክቶችን ሲለዋወጥ በሶስተኛ ወገን ክትትል እንደማይደረግበትም ነው ኩባንያው የገለጸው።
ከዚህም ባሻገር የማህበራዊ ትስስር ገጹ ለትርፍ ባልተቋቋመ ድርጅት የተከፈተ በመሆኑ ምንም አይነት የማስታወቂያ አይታይበትም ተብሏል።
ኤለን መስክ ትዊተርን እንደገዛ ሰራተኞችን በመቀነስ እና አወዛጋቢ ውሳኔዎችን ማሳለፉ እንዲሁም የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አካውንት ዳግም መክፈቱ የፈጠረው ውዝግብ ለማስቶዶን ጠቅሞታል።
የትዊተር ተጠቃሚ ደንበኞችን ብቻ ሳይሆን በትዊተር ሶፍትዌሮችን ሲያበለጽጉ የቆዩ ባለሙያዎች ጭምር በእጁ ማስገባት መጀመሩ እየተነገረ ነው።
መስክ የኤሌክትሮኒክ መተግበሪያ ሰሪዎችን ከጨዋታ ውጪ የሚያደርግ ውሳኔ ማሳለፋቸው ባለሙያዎቹ ፊታቸውን ወደ ማስቶዶን እንዲያዞሩ አድርጓል።
ጁንዩ ክዋንግ የተባለው የትዊተርን የሞባይል መተግበሪያ ያበለጸገ ባለሙያ የማስቶዶን አዲስ ሞና የተሰኘ መተግበሪያ ሊሰራ ነው መባሉንም ዘ ቨርጅ ድረገጽ አስነብቧል።
የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ግን ማስቶዶን ትዊተርን የመተካት አቅም እንደሌለው ነው የሚያነሱት።
ማስቶዶን ኤለን መስክ ትዊተርን እንደተረከበ ሰሞን የነበረው ተጠቃሚ እያሽቆለቆለ ሄዷል፤ የደንበኞቹ ቁጥር ሊጨምር የሚችለው ከመስክ አወዛጋቢ ውሳኔ ጋር በተያያዘ ብቻ ነው በማለት ይሞግታሉ።
በህዳር ወር አጋማሽ ከ650 ሺህ በላይ ከትዊተር የፈለሱ እለታዊ ተጠቃሚዎችን ማፍራት ችሎ የነበረው ማስቶዶን አሁን ላይ እለታዊ ደንበኛው ከ130 ሺህ ያልበለጠ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ማስቶዶን እንደ ትዊተር ከአንድ ማዕከል ቁጥጥር የማይደረግበት መሆኑ ግን ወደፊት ተመራጭ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ሊያደርገው እንደሚችል ይገመታል።