ትዊተር ለታሊባን አባላት የሰጠውን "ሰማያዊ ባጅ" ማስወገድ ጀመረ
የታሊባን አባላት ትዊተርን መጠቀም የጀመሩት የቡድኑ የፖለቲካ ቢሮ በ2012 በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ሲቋቋም ነበር
ትዊተር እርምጃውን የወሰደው የትዊተር ተጠቃሚዎች ባቀረቡት ተቃውሞ ነው
አዲሱ የትዊተር ባለቤት ኢለን መስክ ከወራት በፊት የማህበራዊ የትስስር ገጹ ተጠቃሚዎች ማንነታቸውን የሚያረጋግጠውን "ሰማያዊ ባጅ" ምልክት መግዛት እንደሚችሉ ሲያሳውቁ ቀድመው እድሉን ከተጠቀሙት መካከል የታሊባን አባላት ተጠቃሽ ናቸው።
187 ሺህ ተከታይ ያለቸው የታሊባን የመረጃ መምሪያ ኃላፊ ሂዳያቱላህ ሂዳያት፣ 37ሺህ ተከታይ ያለቸው የታሊባን ጠቅላይ ሚኒስትር የጽህፈት ቤት ሃላፊ አህመድ ያሲር እንዲሁም ታዋቂ የታሊባን አመራር እንደሆኑና 411 ሺህ ተከታይ እንዳለቸው የሚነገርላቸው ጄኔራል ሞቢን ካን "ሰማያዊ ባጅ"ን መግዛት ከቻሉ በርካታ የታሊባን ሰዎች መካከል ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም 170 ሺህ ተከታይ ያላቸው የአፍጋኒስታን የመረጃና ባህል ሚንስትር የመገናኛ ብዙኃን ቁጥጥር ኃላፊ አብዱል ሀቅ ሃማድ እና የቀድሞ የታሊባን አመራር የነበሩት ሙሃመድ ጃላል ሰማያዊ ባጅ ማግኘት ችለዋል፡፡
የማረጋገጫ ምልክቱን ያገኙት ሙሃመድ ጃላል “ኤለን መስክ ትዊተርን ዳግመኛ ታላቅ አድርጎታል” ሲሉ ደስታቸው መግለጻቸውን የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጅ የታሊባን ሰዎች ወደ ትዊተር መምጣት ለበርካቶች የሚያስደስት እንደላልሆነ እየተገለጸ ነው፡፡
በርካታ የትዊተር አካውንት ተጠቃሚዎች ለታሊባን አባላት ሰማያዊ የጭረት ምልክት (ባጅ) መስጠት ማለት የተሳሳቱ ዜናዎችን ለማሰራጨት የበለጠ ድፍረት የሚፈጥር በመሆኑ ማቆም እንደሚያስፈልግ ጠይቀዋል።
በርካታ ተቃውሞ ያስተናገደው ትዊተርም የታሊባን ሰዎችን "ሰማያዊ ባጅ" ማገድ መጀመሩ እየተነገረ ነው፡፡
የአፍጋኒስታን የዜና ወኪል አማጅ ኒውስ እንደዘገበው ከአንድ ቀን በፊት ሰማያዊውን መለያ በመግዛት አነጋጋሪ የነበሩት በካቡል የሚገኙት የቀድሞ የታሊባን ደህንነት ቃል አቀባይ ጄኔራል ሞቢን ካን ትዊተር ሰማያዊውን ባጅ ካስወገደባቸው አንዱ ናቸው፡፡
በተጨማሪም ከ1 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሏቸው የቀድሞ የአፍጋኒስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አምሩላ ሳሌህ መለያ ሰኞ ተሰርዟል።
የአምሩላህ ሳሌህ "ሰማያዊ ባጅ" የታገደበት ምክንያት እስካሁን በውል ባይታወቅም የታሊባን አባላት እና ተቃዋሚዎች ማይክ ፖምፒዮ ስለ ዶሃ የሰላም ስምምነት በተናገሩት ዙሪያ በሰጡት የአጸፋ ምላሽ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
ትዊተር ሁሉም ተጠቃሚዎች አጸያፊ፣ ስነ ምግባር የጎደላቸው ወይም ከሽብርተኝነት ጋር የተገናኙ ናቸው ብለው የሚያምኑትን ይዘት ወይም የተጠቃሚ መለያዎች እንዲያሳውቁ የሚፈቅድ በመሆኑ ሰማያዊ ምልክት የተደረገባቸውም ጭምር ሊታገዱ የሚችሉበት እድል ከፍተኛ ነው፡፡
እናም አምሩላህ ሳሌህ የታገዱት የትዊተር ተጠቃሚዎች ቡድን ሪፖርት ባደረገው መሰረት ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው፡፡
የታሊባን አባላት በትዊተር ላይ መገኘት የጀመሩት ከጥቂት አመታት በፊት የቡድኑ የፖለቲካ ቢሮ በ2012 በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ሲቋቋም ነበር፡፡