"X Æ A-12" አጠራሩም ሆነ ትርጓሜው ማነጋገሩን የቀጠለው የኤለን መስክ ልጅ ስም
የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር በ2020 ለተወለደው የመጀመሪያ ልጁ ቁጥርና ምልክቶች ያሉበት ያልተለመደ ስም አውጥቷል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/13/273-184746-gettyimages-2198396004-e1739386318528_700x400.jpg)
የልጁ እናት ካናዳዊቷ አቀንቃኝ ግሪምስ የስሙን ትርጓሜ አብራርታለች
ቢሊየነሩ ኤለን መስክ እና ካናዳዊቷ ታዋቂ ዘፋኝ ግሪምስ የመጀመሪያ ልጃቸውን መውለዳቸውን ይፋ ያደረጉት በግንቦት ወር 2020 ነበር።
ሁለቱ ዝነኞች ልጅ የመውለዳቸው ዜና መነጋገሪያነቱ እንደቀጠለ ለልጃቸው ያወጡት ስም የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ይዟል።
መስክ በወቅቱ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ (በ2022 በገዛ) ገጹ ለተከታዮቹ "እናትና ልጁ ደህና ናቸው" ብሎ ከጻፈ በኋላ ለአዲሱ ልጃቸው "X Æ A-12" የሚል ስም ማውጣቱን ይፋ አድርጓል።
ያልተለመደው ስም ትርጉሙ ምንድን ነው? እንዴትስ ነው የሚጠራው? የሚለውም ሲያጠያይቅ ቆይቷል።
በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሾመው መስክ ከትናንት በስቲያ ልጁን እሽኮኮ ብሎ በዋይትሃውስ የመጀመሪያውን መግለጫ ሲሰጥ ይሄው ስም ዳግም መነጋገሪያ ሆኗል።
የስሙ ህጋዊነት ጥያቄና የተደረገው ለውጥ
የመስክና ግሪምስ ልጅ ስም ይፋ ከተደረገ በኋላ ከካሊፎርኒያ ግዛት የስም አወጣጥ ህግ ጋር የተቃረነ ነው የሚሉ ተቃውሞዎች ተሰምተዋል።
የግዛቷ ህግ የትኛውም ስም ከእንግሊዝኛ ፊደላት ውጭ ምልክቶችና ቁጥሮችን መያዝ እንደሌለበት ይደነግጋል።
ግሪምስ ለህጋዊው ጥያቄ "ሮማን ቁጥሮች ሲታዩ ደስ ይላሉ" በሚል ከስሙ መጨረሻ ላይ ያለውን 12 ቁጥር በሮማን ቁጥር ቀይራ የልጃችን ስም "X Æ A-Xii" ይሆናል ብላለች። ሌሎቹ ፊደላትና ምልክቶች ግን አልተቀየሩም።
የልጁ ስም ትርጓሜ ምንድን ነው?
ግሪምስ ከአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ስላገኘችው ልጅ ስም ትርጓሜ ስትገልጽ፦
"X" በሂሳብ "የማይታወቅ" የሚለውን ይወክላል
"Æ" አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ይወክላል፤ በጃፓንኛም "ፍቅር" የሚል ትርጓሜ አለው
"A-12" ደግሞ ቤተሰቦቼ የሚወዱት የአሜሪካ የቅኝት አውሮፕላን ነው ብላለች። አውሮፕላኑ ፈጥነቱ ወደር እንደማይገኝለት በመጥቀስም "ፈጠነ" ወደሚለው የአማረኛ ስም የሚቀራረብ ትርጉም ሰጥታዋለች።
"X Æ A-12" እንዴት ነው የሚነበበው?
ይህ አስቸጋሪ ስም እንዴት እንደሚጠራ እንኳን ሌላው ህዝብ ወላጆቹ እና የቅርብ ቤተሰቦቹ እስካሁን ተመሳሳይ ምላሽ አይሰጡም።
እናቱ ግሪምስ ትክክለኛው የስሙ አነባበብ በእንግሊዝኛ "X" ከ"A" በፊት ስትመጣ አይነት (እንደ "exam") ነው ትላለች። በእርሷ አገላለጽ ስሙ "ዛኤ12" ወደሚለው ይቀርባል።
ኤለን መስክ ግን ዝባዝንኬ ሳይበዛ "ኤክስ" ብሎ መጥራት ይችላል ይላል። "Æ"ን አሽ ብሎ ማንበብ እንደሚቻልም ያነሳል።
አወዛጋቢው ስም ከአራት አመት በኋላም መነጋገሪያነቱን የቀጠለ ሲሆን በአለማችን ለሰዎች ከተሰጡ አስገራሚ ስሞች መካከል ተካቷል። ከህግ አንጻር ግን የስሙ ዘላቂነት አጠያያቂ ነው።
ኤለን መስክ ከካናዳዊቷ አቀንቃኝ ክሌር ቡቸር (ግሪምስ) ጋር ከ2018 ጀምሮ የፍቅር ግንኙነት የጀመረ ሲሆን፥ በ2021 በይፋ መለያየታቸውን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።