ኢለን መስክ መንግስት አላግባብ የሚያወጣውን ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ማስቀረት እንደሚችሉ ተናገሩ
ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፈ መንግስታዊ ሀላፊነት ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል
በስልጣን ላይ ያለው የባይደን- ሀሪስ አስተዳድር ከ6 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ አባክኗል ተብሏል
ኢለን መስክ መንግስት አላግባብ የሚያወጣውን ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ማስቀረት እንደሚችሉ ተናገሩ።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ ከቀናት በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ታካሂዳለች።
ምርጫው ከአሜሪካ ባለፈ በዓለም ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚባለው ይህ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከወዲሁ እጩዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ቀጥለዋል።
የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ መሆናቸውን ያወጁት የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋው ኢለን መስክ የአሜሪካዊያን ግብር ከፋዮች ገንዘብ ያላግባብ እየባከነ መሆኑን ተናግረዋል።
በፔንሲልቫኒያ በተካሄደ የዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ኢለን መስክ የፕሬዝዳንት ባይደን እና ምክትላቸው ካማላ ሀሪስ አስተዳድር በተያዘው 2024 ዓመት ውስጥ 6 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል ብለዋል።
እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ከሆነ ይህ ኢለን መስክ ከህ የመንግስት የተጋነነ ወጪ ውስጥ ቢያንስ 2 ትሪሊዮን ዶላር መቀነስ እችላለሁ ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን ካሸነፉም "የመንግስት ውጤታማነት* የሚባል ተቋማን ለመምራት ፈቃደኛ ነኝ፣ ለዚህም ደመወዝ አልፈልግም ሲሉም መናገራቸው ተገልጿል።
የሰሞንኛውን የምረጡኝ ቅስቀሳን ተከትሎ በተሰራ የቅድመ ምርጫ ውጤት የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ከዲሞክራቷ ካማላ ሀሪስ የ10 በመቶ እና በላይ ብልጫ አሳይተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ የክሪፕቶከረንሲ ግብይትን እደግፋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ የዚህ ደጋፊ የሆነ ሰዎች ድጋፋቸውን ለትራምፕ እንሰጣለን ከማለታቸው ባለፈ የቢትኮይን ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።