አልጄሪያዊቷ ቦክሰኛ በዶናልድ ትራምፕና በኢለን መስክ ላይ በሳይበር ትንኮሳ ክስ መሰረተች
አወዛጋቢዋ ቦክሰኛ በፓሪሱ ኦሎምፒክ ላይ በማህበራዊ ትስስር ገጽ መብቴን የሚገፋ ትንኮሳ አድርሰውብኛል ብላለች
ቦክሰኛዋ ክሱን የከፈተችው ከጥላቻ ንግግር እና ከሳይበር ትንኮሳ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ለሚመለከተው የፓሪስ ፍርድ ቤት ነው
አልጄርያዊቷ ቦክሰኛ ኢማን ከሊፍ፤ በማህበራዊ ትስስር ደርሶብኛል ላለችው ትንኮሳ የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፣ ኢለን መስክ እና ብሪታናዊቷን ደራሲ ጄኬ ሮውሊንግ ላይ ክስ መስርታለች።
በዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ መነጋገርያ ከሆኑ አትሌቶች መካከል እንዷ የሆነችው ኢማን በኦሎምፒክ የሴቶች የቦክስ ውድድር የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ሆናለች።
አትሌቷ ሴት ሆና እንደተወለደች እና እድሜዋን በሙሉ ሴት ሆነ እንደኖረች በተደጋጋሚ ብታሳውቅም በማህበራዊ ትስስር ገጾች ከሚደርስባት ትችት እና ትንኮሳ አላመለጠችም፡፡
ብሪታንያዊቷ ታዋቂ ደራሲ ጄኬ ሮውሊንግ ኢማንን በወንድ ጾታ “አንተ” እያለች በመግለጽ የተለያዩ ጽሁፎችን በኤክስ ገጽ ላይ ያሰፈረች ሲሆን ቢሊየነሩ ኢለን መስክ በበኩሉ “ወንዶች በሴቶች ዘርፍ ውስጥ እንዲወዳደሩ መፈቀዱ ያስገርማል” ሲል ትችት አዘል ሀሳቡን በኤክስ ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከኢማን የጾታ ሁኔታ ጋር የተናገሩት ንግግር በይፋ ባይገለጽም በክስ መዝገቡ ውስጥ ስማቸው ተካቶ ቀርቧል፡፡
የአትሌቷ ጠበቃ ናቢል ቦዲ የክስ መዝገቡን መቀመጫውን በፓሪስ ላደረገው ከጥላቻ ንግግሮች እና ከሳይበር ትንኮሳዎች ጋር የተያያዙ ክሶችን ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ማስገባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
አትሌቷ ላይ የመብት ጥሰት ፈጽማዋል የተባሉት ግለሰቦች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከ2-5 አመት እስር አልያም ከ10 ሺህ ዩሮ በላይ ቅጣት የሚተላለፍባቸው ይሆናል ተብሏል፡፡
ተከሳሾቹን በተገቢው መንገድ ተጠያቂ ለማድረግ በስም ከተጠቀሱት ግለሰቦች በተጨማሪ የኤክስ ኩባንያም በክሱ ውስጥ መካተቱን ያስረዱት ጠበቆቹ ተቋሙ መሰል የጥላቻ ንግግሮችን አይቶ እንደላየ በማለፉ ቀዳሚ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡
አልጄርያዊት ቦክሰኛ ኢማን ከሊፍ በፓሪሱ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆኗ ይታወሳል፡፡
በአምስት ዙር በተደረገው ግጥሚያ ኢማን በዳኞች ውሳኔ ቻይናዊቷን የአለም ሻምፒዮና ያንግ ሊዩን በማሸነፍ ነው የወርቅ ሜዳልያውን ያጠለቀችው፡፡
ኢማን ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየት በጾታዋ ምክንያት እየደረሰባት የነበረው ጫና በውድድሩ እንድትበረታ እና አሸናፊ እንድትሆን እንዳስቻላት ተናግራለች፡፡
የፓሪሱን ኦሎምፒክ ውድድር ጨምሮ ተከታታይ 13 ግጥሚያዎችን ማሸነፍ የቻለችው እና ላለፉት ስምንት አመታት የቦክስ ውድድሮችን ስታደረግ የቆየችው ኢማን ከአራት ዓመታት በፊት በተደረገው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ነበረች።